ቀጥታ፡

አፍሪካ ካንሰርን ለመከላከል መመሪያዎችን ወጥ ማድረግና በጋራ መስራት ይገባታል

አዲስ አበባ ነሐሴ 22/2011 አፍሪካ የካንሰር በሽታን ለመከላከል የሕክምና መመሪያዎችን ወጥ ማድረግና በጋራም ገቢራዊ ማድርግ እንደሚገባት ተገለጸ። የአፍሪካ  ካንሰር ጥምርት  ጉባዔ ካንሰርን ለመከላከል ከተለያዩ የአህጉሪቷ ክፍል የተውጣጡ አገራት ዛሬ በአዲስ አበባ ምክክር እያደረጉ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚያመለክተው በዓለም ላይ ለሞት ሊዳርጉ ከሚችሉ በሽታዎች መካከል ካንሰር የሁለተኛ ደረጃን ይይዛል። እ.አ.አ 2018 ዘጠኝ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዜጎች በዚሁ በሽታ እንደሞቱ መረጃዎቹ ያመለክታል። በጉባኤው መክፈቻ የአፍሪካ ካንሰር ጥምርት ጉባኤ አስተባባሪና የናይጀሪያ ጤና ሚኒስትር  ፕሮፌሰር አይሳክ አዴወሌ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት አፍሪካን ከካንሰር ነጻ ለማድረግ የካንሰር ህክምና መመሪያዎች ወጥነት እንዲኖራቸው በማድረግና ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ የተወሰኑ አገራት መመሪያዎቹን ተግባራዊ እያደረጉ እንደሆነ የተናገሩት ፕሮፌሰር አይሳክ፤ ሌሎችም ይህንን ፈር ተከትለው በትብብር ትግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። “በአሁኑ ወቅት በአህጉሪቷ  የካንሰር በሽታ እየጨመረ በመሆኑ ባሉት የህክምና ቁሳቁሶችና ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተን ሊንሰራበት ይገባለም” ብለዋል። እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ የካንሰር ሕክምና መመሪያዎች ነባራዊ ሁኔታንና ባሉት ቁሳቁሶችን በመጠቀም ቀልጣፋ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል። በዓለም አቀፍ የካንሰር ምርምራ ቴክኖሎጂ ማሻሻል(አይ ቢ ኤም) ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰሎሞን አሰፋ በበኩላቸው የካንሰር በሽታን ምርመራ ለማቃለል የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችንና መመሪያዎችን በማዘጋጀት  ህክምና ማዕከላት በመስጠት አብረው  እየሰሩ መሆኑን ያብራራሉ። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በምርምራ ወቅት የሚከናወኑ ሒደቶችን ለማቀላጠፍ ያግዛል ያሉት ዶክተር ሰሎሞን በቀጣይም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች አጋራት ጋር ለመስራት እቅድ እንዳላቸው ይናራሉ። የአሜሪካ ካንሰር ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋሪይ ሬዲ በበኩላቸው በአፍሪካ የካንሰርን በሽታ ለመከላከል ሁሉም አገራት በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ማህበሩ ካንሰርን ለመከላከል ካካበተው ከፍተኛ ልምድ ለአህጉሪቷ ለማካፈልና አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ያብራራሉ። የካንሰር በሽታን በዘላቂነት ለመከላከል በተለይም የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግና የባለሙያ ማህበሩ እገዛ እንደሚያደረግም ይገልጻሉ። በጉባኤው የተገኙት የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ካንሰርን ለማከላከል አገሪቷ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን ጠቁመው ግንዛቤ የማሳደጉና የሕክምና ባለሙያዎችን የማጠናከር ስራዎችን እየሰራች ነው ብለዋል። ለካንሰር በሽታ መንስኤ የሆኑትን የትንባሆና ሲጋራ ማጨስ ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች የሚከለክል አዋጅ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በጉባኤው ላይ 100 የሚሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የጤና ሚኒስትሮችና ተወካዮች ለሶስት ቀን የሚቆይ ምክክር በአዲስ አበባ እያደረጉ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም