የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት አገሪቱን የከፋ አደጋ ላይ እንዳይጥላት እርምጃ እየተወሰደ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 22/ 2011 በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ ሁኔታ የከፋ አደጋ ውስጥ እንዳይጥለው መንግስት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያስታወቁት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰነድ ላይ እየመከረ ባለው መድረክ ላይ ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት፤ መንግስት ባለፈው አንድ አመት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ዘርፎች ላይ የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው። አገሪቱ ባለፉት 15 ዓመታት ባለሁለት አሃዝ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት የማስመዝገቧን ያህል የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትም በስፋት እያጋጠማት እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ይህም የአገሪቷን ኢኮኖሚ የከፋ አደጋ ውስጥ እንዳይጥለው መንግስት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ለዚህም መንግስት አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰነድ ማዘጋጀቱን የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰነዱ በዘርፉ ከዚህ በፊት የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠልና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያችል ነውም ብለዋል። የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የአገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች ያብራሩ ሲሆን ከውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ከውጭ ዕዳ ክምችት፣ ከዋጋ ግሽበት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አገሪቱ እየገጠሟት ያሉትን ፈተናዎች ያሉ ችግሮችን ዘርዝረዋል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ካለባቸው አገሮች ተርታ መቀመጧን ዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም (IMF) እና የዓለም ገንዘብ ድርጅትን ጠቅሰው ተናግረዋል። አገሪቷ ለከፍተኛ የዕዳ ጫና የተዳረገችው በበርካታ ምክንያቶች መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር እዮብ  'ደካማ የውጭ ንግድ አፈጻጸምን' ለአብነት አንስተዋል። የውጭ ምንዛሬ እጥረትም የአገሪቱ መገለጫ እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት ሚኒስትር ዲኤታው ይህም  ሌላኛው የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮት ነው ብለዋል። ይህም የውጭ ባለኃብቶች ባሰቡት ልክ ወደስራ እንዳይገቡ እያደረጋቸው ነው ሲሉ ገልፀዋል። የዋጋ ግሽበትም ምጣኔ ኃብቱን እየተፈታተነ ያለ ሌላው ችግር መሆኑንም አመልክተዋል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉት የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተናዎች የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ ሁኔታ የከፋ አደጋ ውስጥ እንዳይከቱት መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰነድ አዘጋጅቷል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የህዝቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ነው የሚተገበረው ሲሉም  ሚኒስትር ዲኤታው ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የአገሪቱ ዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ በሶስት እጥፍ ማደግ ይጠበቃል ብለዋል። በመላው ኢትዮጵያ ከ40-45 ሚሊዮን ዜጎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንደሚያስፈልጋቸውም ዶክተር እዮብ አስታውቀዋል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በቀጣይ በትኩረት መስራት ይገባልም ሲሉ አስገንዝበዋል። በውይይቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በስብሰባው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራው ዘላቂና የተረጋጋ እንዲሆን ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን አንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም