በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የኢትዮጵያን ተግባር ተመድና የአውሮፓ ህብረት አደነቁ - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የኢትዮጵያን ተግባር ተመድና የአውሮፓ ህብረት አደነቁ
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 22/ 2011 ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት የያዘችውን አቋም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና የአውሮፓ ህብረት አደነቁ። አገሪቷ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ በተግባር የሚታዩ የልማት ስራዎች በማከናወን ላይ መሆኗን አመልክተዋል። በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ልኡክ የልማት ትብብር ሃላፊ ዔሪክ ሀበርስ እንዳሉት ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን በማከናወን ቁርጠኛ አቋም ይዛ በመስራት ላይ ትገኛለች። በዚህም ተግባሯ በአፍሪካ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ መሆኗንና ያደጉ አገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የካርበን መጠን እንዲቀንሱ አቋሟን በግልፅ እያራመደች ያለች ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል። "በኢትዮጵያ በብዛት የተተከሉ ችግኞች ተገቢው እንክብካቤ ተደርጎላቸው እንደሚፀድቁ አምናለሁ" ያሉት ሃላፊው ለዚህም ህብረቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። ከኢፌዲሪ የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጋር የረዥም ጊዜ ትብብር መኖሩን አስታወሰው ኢትዮጵያ ቀጣይ በዘርፉ ለምታደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎች የ14 ሚሊዮን ዩሮ የበጀት ድጋፍ ለማድርግ ታስቧል ብለዋል። በተለይም የግሉ ዘርፍ የከባቢ አየር ብክለትን በመቀነስ በኩል የድርሻውን እንዲወጣ በማድርግ ሂደት ድጋፍ ይደረጋልም ነው ያሉት። በኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ስቴቨን ዌር ኦማሞ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት የድርሻዋን እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል። አገሪቷ በዘረፉ ልማት ስትራቴጂ ቀርፃ በመተግበር ግንባር ቀደም መሆኗንም ተናግረዋል።