ኢትዮጵያ የ"ስዊች አፍሪካ ግሪን ፕሮግራም" አባል ሆነች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የ"ስዊች አፍሪካ ግሪን ፕሮግራም" አባል ሆነች
አዲስ አበባ ነሀሴ 22/2011ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን በመደገፍ ዓላማ ላይ የተቋቋመው የ"ስዊች አፍሪካ ግሪን ፕሮግራም" አባል ሆነች። መርሃ ግብሩ በዋናነት በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግና ተረፈ ምርት አወጋገድና አስተዳደር ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ ሲሆን፤ በተባበሩት መንግስታትና በአውሮፓ ህብረት ይደገፋል። ቦርኪናፋሶ፣ ጋና፣ ሞሪሺየስ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካና ኡጋንዳ ቀደም ብለው የነበሩ የመርሃ ግብሩ አባል አገራት ሲሆኑ፤ ዛሬ በአዲስ አበባ በተጀመረው የፕሮግራሙ ጉባዔ ኢትዮጵያ 7ኛ አባል ሆና መቀላቀሏ ተገልጿል። ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባዔ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተወከሉ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ናቸው። ለመርሃ ግብሩ የቀጣይ ሶስት ዓመታት ማስፈጸሚያ 20 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡም ይፋ ሆኗል። ከዚህም ወስጥ 3 ሚሊዮን ዩሮ ወይም ወደ መቶ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለኢትዮጵያ የተመደበ ነው። የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ የፕሮግራሙ አባል መሆኗ በአረንጓዴ ልማት ላይ እየተገበረች ላለው ስራ ትልቅ አቅም ይፈጥርላታል። ፕሮግራሙ በቀጣይ የአረንጓዴ ልማቱን በሚደግፉ ተግባራት ላይ የግሉና የመንግስት ዘርፍ ተቀናጅተው እንዲሰሩም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት። ይህን ስራ ለማሳለጥም ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጠናከረ ስራ ይሰራል ብለዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ሚስተር ስቴቬን ዌር ኦማሞ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ረገድ በአብነት የምትጠቀስ አገር መሆኗን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላይ ያስቀመጠችው ግብ እንዲሳካ የተባበሩት መንግስታት በተጀመረው ፕሮግራም በኩል የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል። የስዊች አፍሪካ ግሪን ፕሮግራም በየሦስት ዓመቱ እየታደሰ ስራ ላይ የሚውል ነው። ቦርኪናፋሶ፣ ጋና፣ ሞሪሺየስ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካና ኡጋንዳ ቀደም ብለው የነበሩ አባላት ሲሆኑ ኢትዮጵያ በ7ኛ አባልነት ተቀላቅላቸዋለች። የስዊች አፍሪካ ግሪን ፕሮግራም በየሦስት ዓመቱ እየታደሰ ስራ ላይ የሚውልነው።