ዘመናዊ ህክምናን ከመንፈሳዊ ህክምና ጋር የማስተሳሰር ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናዊ ህክምናን ከመንፈሳዊ ህክምና ጋር የማስተሳሰር ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል
ነሀሴ 21/2011 ዘመናዊ ህክምናን ከመንፈሳዊ ህክምና ጋር በማስተሳሰር ለህሙማን የተሻለ ፈውስ ማምጣት የሚቻል በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለፀ። የሃይማኖት መሪዎችና መንፈሳዊ አባቶች በአለርት ህክምና ማዕከል የሚገኙ ህሙማንን ጎብኝተዋል፤ ለህሙማኑም መንፈሳዊ አገልግሎት ሰጥተዋል። ማዕከሉ የህክምና አሰጣጡን ከመንፈሳዊው ጋር ማስተሳሰር የሚያስችል ሳምንት “አብሮነት፣ ርህራሄና ስነ-ምግባርን በተላበሰ የህክምና አገልግሎት መስጠት” በሚል መሪ ሐሳብ ሁለተኛ የጉብኝት ሳምንት ዛሬ ጀምሯል። የኦርቶዶክስ፣ የእስልምና እና የካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን የኃይማኖት አባቶች በጉብኝቱ የተገኙ ሲሆን ፅኑ የህሙማን መታከሚያ የድንገተኛ አደጋ ክፍልን፣ የማዋለጃና የቀዶ ጥገና ክፍሎችን ጎብኝተዋል። አባቶቹ በጉብኝቱ ወቅት ህሙማንን አፅናንተዋል፣ እንደየዕምነታቸው የቡራኬና የፀሎት አገልግሎትም ሰጥተዋል። የህክምና ባለሙያዎች ከታካሚው ጋር በቅርበት መስራታቸው ለጉብኝቱ መጀመር ምክንያት ነው ያሉት የማዕከሉ ዋና ስራ እስኪያጅ አቶ ዳኛው አግዘው ወደፊትም የታካሚውን መንፈሳዊ እርካታ በመፍጠር ዘመናዊ ህክምናውን ማገዝ የሚያስችሉ ስራዎች በማዕከሉ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። መንፈሳዊ ህክምና የሰው ልጅ እንደየእምነቱ በፈጣሪ በማመን የሚጀምር ሆኖ ለሌላው መኖርንና በጎ ነገር ማድረግን የሚጨምር ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ የኃይማኖት እና የህክምና ተቋማትና አላማቸው ሰብዓዊ ፍጡር ላይ በመሆናቸው በጥምረት ቢሰሩ የህክምና አሰጣጡን ሙሉ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል። እንደብጹዑ ገለጻ፤ ዘመናዊ ህክምና ወደ አገራችን ከመግባቱ በፊት ቤተ-ክርስቲያኗ ወደ ህክምና ተቋማቱ አባቶችን እየላከች “ታምሜ ጠይቃችኋልና …” የሚለውን እምነታዊ ትዕዛዝና ሐዋርያዊ ተልዕኮ የመፈፀም ተሞክሮ ቢኖራትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መቋረጡን ግን አንስተዋል። እንዲሁም ቤተክርስቲያኗ ህሙማንን በጸበል፣ በጸሎትና በመንፈሳዊ ቃል በመፈወስ መንፈሳዊና ሰብዓዊ ግዴታዋን ትወጣ እንደነበርም በጉብኝታቸው ወቅት አንስተዋል። የሰው ልጅ ህክምናዎች ሁሉ በትልቅነቱ የሚታወቀው የአዕምሮ ህክምና እንደሆነ የተናገሩት ብጹዑ፤ በስነ-አዕምሮ መዛባትና መረበሽ ጋር ተያይዞ መፍትሄ ለማግኘት ቅርቡ ይኽው እንደሆነም ነው የሚገልጹት። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ተወካይ ሲስተር ስንቅነሽ ገብረመስቀል በበኩላቸው አካላዊ ህመም በመድሃኒት ሊፈወስ ቢችልም ስነ-ልቦናዊ የሆኑትን ከዘመናዊው ህክምናው ጎን ለጎን እንደየእምነታቸው መንፈዊ አገልግሎት ቢያገኙ ለመፍትሄ ቅርብ ይሆናሉ ብለዋል። የኃይማኖትና የህክምና ተቋማትን በማስተሳሰር ለህሙማኑ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ የህክምና አገልግሎት አሰጣጡ ማዕከሉን ለሌሎችም ተምሳሌት እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ በአፍሪካ የመጀመሪያው ተቋም እንደሚያደርገውም ሲስተር ስንቅነሽ ጠቁመዋል። እንዲሁም መንፈሳዊ ህክምና በማመን የሚሰጥ በመሆኑ ችግሩ የከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ታካሚው እንደየእምነቱ አገልግሎቱን ማግኘት የሚችልበትን ተቋማዊ ትስስር በመዘርጋት ፈጣን ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል አስተያየትም አላቸው። የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሀመድ አብዶ እንደዚሁ የሃይማኖት አባቶች ለታካሚዎች የሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት ችግሩን ከመጋራት አልፎ ሰብዓዊ አገልግሎት እንደሚያሳድገው ገልጸዋል። ስለሆነም ህሙማንን መንከባከብ የሁሉም መንፈሳዊ ግዴታ መሆኑንና ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች መስፋፋት እንዳለበትም ይመክራሉ። የኃይማኖት አባቶቹ ተግባር ወደ ሌሎች ሆፒታሎች መስፋፋት እንዳለበትና እነሱም ከመጠየቃቸው በፊት ጠይቀው መንፈሳዊ አገልግሎቱን ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።