ኢትዮጵያ ከደን ምርቶቿ ተጠቃሚ አለመሆኗ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከደን ምርቶቿ ተጠቃሚ አለመሆኗ ተገለጸ
ነሀሴ 21/2011ኢትዮጵያ ከደን ምርቶቿ የምታገኘውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በዘርፉ ያሉበትን ማነቆዎች መፍታት እንዳለባት ተገለጸ:: "ዘላቂ የደን አስተዳደር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ" በሚል ከሁለት ዓመት በፊት የተቀረጸው የጥናትና ምርምር ፕሮጀከት መጠናቀቁን በማስመልከት የማጠቃለያ አውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል። ፕሮጀክቱ በስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ(ሲዳ) የፋይናንስ ድጋፍ ሲተገበር የቆየ ሲሆን ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ እያከናወነች ያለችውን ስራ በጥናትና ምርምር በማገዝ ዘላቂ የደን ልማት ስራው ውጤታማ እንዲሆን መደገፍ ነው። በፖሊሲ ጥናቶች ኢንስቲትዩት የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ጥናት ማዕከል፣ የኢትዮጵያ አካባቢ የደን ጥናት ኢንስትቲዩት እንዲሁም የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ፕሮጀክቱን ሲተገብሩ የቆዩ ተቋማት ናቸው። በዓለም አቀፍ የደን ምርምር ተቋም የኢትዮጵያ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሀብተማርያም ካሳ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጥሮ ደን አስተዳደርን ተጠቅሞ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የማሳደግ ልምድ በሚፈለገው ደረጃ እየተሰራበት እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። በመንግስት ደረጃ የደን ልማት በዋነኛነት የትኩረት አቅጣጫው የደን ሽፋንን ከማሳደግና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው አንጻር በቂ ትኩረት አለማግኘቱን ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት በአሳታፊ የደን አስተዳደር ህብረተሰቡ ከደን ልማት የሚያገኘው ገቢ አነስተኛ በመሆኑ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱም ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል። የደን ምርት ለኢኮኖሚ ያለውን ጠቃሜታ እንዲሁም ያሉት የገበያ እድሎችን አስመልክቶ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑንና በዚህም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የመሬት አጠቃቀምና ይዞታ ፖሊሲ እና እቅድ የሌላት መሆኑ፣የደን ተቋማትና የኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላት የቅንጅት አሰራር ክፍተት ያለበት መሆኑ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የፋይናንስ አቅርቦት ላይ ያሉ ችግሮች ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ ማነቆ ናቸው። በእውቀትና ፈጠራ ላይ ተመስርቶ የደን ምርቶችን ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ያለው ስራ በቂ አንዳልሆነና በአጠቃላይ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ነው ዶክተር ሀብተማርያም ያስረዱት። በሀዋሳ ዩንቨርስቲ የወንዶ ገነት የደንና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ መምህር ዶክተር የምሩ ተስፋዬ በኢትዮጵያ በደን ልማት ላይ የተሰማሩ ዜጎች አብዛኛውን ገቢ የሚያገኙት እንጨት ነክ ካልሆኑ ምርቶች እንደሆኑ ገልጸዋል። ማር፣ ዕጣን፣ሙጫ፣ቅመማ ቅመሞችና የደን ቡና ዋነኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ገልጸው እነዚህ ምርቶች በየዓመቱ ማግኘት የሚቻሉ ምርቶች እንደሆኑ አመልክተዋል። ያም ቢሆን የትራንስፖርት አቅርቦት በሚፈለገው ደረጃ ባለመኖሩ ምክንያት ዜጎች ምርታቸው በሚኖሩበት አካባቢ እንደሚሸጡና የሚያመርቱት የደን ውጤት ወደ ከተሞች ሄዶ በትልቅ ዋጋ እንዳይሸጥ እንቅፋት እንደሆነባቸውም ጠቅሰዋል። በደን ምርት የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አካላት ብዙ በመሆናቸው አምራቹ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ እየሆነ አለመሆኑና የእንጨት ኢንዱስትሪው በሚፈለገው ደረጃ አለማደግ ለእንጨት ምርት በሚፈለገው ደረጃ ግብአት እየቀረበ እንዳልሆነም ገልጸዋል። ደንን ለኢኮኖሚ ልማት መጠቀምና ደን የመጠበቅና የመንከባከብ ሁኔታም ሚዛናዊ በሆነ መልኩ መታየት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል። የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ዘርፍ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ተፈራ መንግስቱ እንደሚሉትም መንግስት በደን ምርት የእሴት ሰንሰለት ያሉ አላስፈላጊ አካላትን በመቁረጥ ሰንሰለቱን ማሳጠር ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በደን ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ በመሸጥ ገቢ ማሳደግና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራም ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም ገልጸዋል። የእንጨት ምርቶች ግብአትን ለማሳደግ በደን አዋጅ ውስጥ ደን በመቁረጥ ንግድ ጥቅም ላይ ማዋል የሚከለክል በመሆኑ አዋጁ የደን ሽፋንን በማይጎዳ ሁኔታ ያረጁ ዛፎችን ቆርጦ መጠቀም የሚቻልበት ሁኔታ ቢኖር በዘርፉ ባለሙያዎች የሚቀርቡ ሀሳቦች በመንግስት ይታያሉ ብለዋል። በአጠቃላይ የተነሱ ችግሮችንና ማነቆዎች በዘርፉ ያሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ያሉ የአሰራር ክፍቶችን በመፈተሽ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መንግስት በትብብር እንደሚሰራም አክለዋል። በማጠቃለያ አውደ ጥናቱ ደንና የኢኮኖሚ ጠቀሜታው፣የደን ዘርፍ ፖሊስና ስትራቴጂዎች ለዘላቂ ደን አስተዳደር ያላቸው ሚና፣የደን ምርት ላይ እሴቶችን ጨምሮ መጠቀም ያለው ጠቀሜታና ዘላቂ የደን አስተዳደርና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ በሚሉ ርዕሶች የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የጥናትና ምርምር ውጤቶቹ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለውሳኔ ሰጪዎች በግብአትነት እንደሚያገለግሉም ተገልጿል። የስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ ለዘላቂ የደን አስተዳደር በአጠላይ ለደኑ ዘርፍ የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ አጠናክሮ እንሚቀጥልም ገልጿል። የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የስራ ሃላፊዎች ፣የደን ተመራማሪዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።