ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያሰባሰበውን ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ የመማሪያ ደብተር ለከተማ አስተዳደሩ አስረከበ

ነሀሴ 21/2011 የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በከተማው የሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን የትምህርት ቁሳቁስ ችግር ለማቃለል ከተለያዩ ድርጅቶች ያሰባሰበውን ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ የመማሪያ ደብተር ለከተማ አስተዳደሩ አስረከበ። ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ የተማሪዎችን የመማሪያ ደብተርና ቁሳቁስ ችግር መቀነስ ይቻል ዘንድ ያቀረበውን  የበጎ ተግባር ጥሪ ተከትሎ ነው ከስምንት መንግስታዊና የግል ድርጅቶች የተበረከተለትን 1 ሚሊዮን 835 ሺህ  ደብተር  በዛሬው እለት ለከተማ አስተዳደሩ ያስረከበው። ምክትል ከንቲባ ኢንጂኒየር ታከለ ኡማ ለመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚታደለውን ደብተር ዛሬ በተከናወነ ስነ-ስርዓት ተረክበዋል። የጉራጌ ልማት ማህበር አንድ ሚሊዮን ደብተር በመስጠት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል። ከዚህም ሌላ ህብረት ባንክ 200 ሺህ፣ ጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ 200 ሺህ፣  ዳሽን ባንክ 100ሺህ፣ ንብ ባንክ 120 ሺህ እንደዚሁም የኢትዮጵያ ኮንትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን  100 ሺህ ደብተር ድጋፍ አበርክተዋል። የኮሚሽኑ ሰራተኞች በበኩላቸው 105 ሺህ ደብተር ሲያበረክቱ የአዲስ አበባ  እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል 10 ሺህ ደብተር  ሰጥተዋል። ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ከርክክቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር ከበጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር በመሆን የተቸገሩ ተማሪዎችን እና ወላጆችን ለመደገፍ የሚካሄደውን እንቀስቃሴ  ለማጠናከር በትጋት እየተሰራ መሆኑን  ገልጸዋል። በበጎ ተግባሩ እየተሳተፉ ላሉ የግልና የመንግስት ተቋማትም  ምስጋና አቅርበዋል። የደብተር ድጋፉን ያበረከቱት ድርጅቶች ተወካዮች ለኢዜአ እንደገለፁት ህፃናትን ማስተማርና መደገፍ ከምንም በላይ የተቀደሰ በጎ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው በበጎ አገልግሎቱ በመሳተፋቸው ደስታ እንደተሰማቸዉ ገልፀዋል። አክለውም የዚህ ዓይነቱ ተግባር አገር ተረካቢ መልካም ዜጋ በመፍጠር አገርን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር የሚስችል በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። ወደፊትም በከተማው ለሚከናወኑት የበጎ አገልግሎት ስራዎች ለሚቀርብላቸው ጥሪ ምላሽ ለመስጠት የተቻላቸዉን እንደሚያደርጉም ገልፀዋል። የደብተር ድጋፉ በገንዘብ 20 ሚሊዮን ብር ይገመታል። የተለያዩ ተቋማት ተመሳሳይ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም