የተጀመረው አገራዊው የግብር ንቅናቄ መርሃ ግብር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመረው አገራዊው የግብር ንቅናቄ መርሃ ግብር ተጠናክሮ ይቀጥላል
ነሀሴ 21/2011 በኢትዮጵያ የግብር አሰባሰብን ለማሳደግ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመላው አገሪቱ የተጀመረው የግብር ንቅናቄ በመጪው ዓመትም አዳዲስ ኩነቶችን በማካተት እንደሚቀጥል የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ። በኢትዮጵያ ግብር መክፈል አለበት ተብሎ ከሚታሰበው ማህበረሰብ መካከል የሚጠበቅበትን እየተወጣ የሚገኘው 60 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው። የገቢዎች ሚኒስቴር ከዘርፉ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉትን እነዚህን የመሰሉ ችግሮች በመቀነስ አገራዊውን የግብር መሰብሰብ አቅም ማጎልበት ይቻል ዘንድ እየወሰዳቸው ካሉት እርምጃዎች መካከል በግብር መክፈል ዙሪያ ያለውን አነስተኛ የዜጎች ግንዛቤ ማሳደግ አንዱ ነው። የሚኒስቴሩ ኮሚኒኬሽን ዳሬክተር ወይዘሮ ኡሚ አባጀማል ለኢዜአ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከምጣታመነጨው ምጣኔ ሃብት አኳያ መሰብሰብ ያለባትን ገቢ ለማሳካት በዜጎች ግንዛቤ ላይ መስራት ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነው። በዚህም መሰረት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መንግስት ተግባራዊ ካደረጋቸው አሰራሮች መካካል የግብር ንቅናቄው አንዱ እንደነበር አውስተዋል። ከግብር ከፋዩ ጋር የተካሄዱት የውይይት መድረኮች፣ ስፖርታዊ ሁነቶችና ግብር ከፋዩን ማህበረሰብ ለማበረታታት የተዘጋጁት የእውቅና መርሃ ግብሮች በ2011 ዓም የተከናወነው የግብር ንቅናቄ አካላት ነበሩ። ዘርፉን ለማጠናከር እንዲቻል የምሁራን ውይይቶች መካሄዳቸውም እንደዚሁ። በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ግብር ከፋይና ለታክስና ለጉምሩክ ህግ ተገዠ የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር የንቅናቄው ዓላማ እንደሆነም ወይዘሮ ኡሚ ተናግረዋል። በዚህም በንግዱ ማህበረሰብና አገልግሎት በሚሰጠው ዘንድ የግንዛቤ መሻሻል መመዝገቡን ገልፀዋል። በበጀት ዓመቱ የተሻለ ገቢ መሰብሰብ ካስቻሉት የተለያዩ ምክንያቶች ውስጥ የግብር ንቅናቄው እንደሚጠቀስ ተናግረዋል። የንቅናቄው ግብ ግብር መሰወር ፀያፍና አስነዋሪ ተግባር ከመሆኑም በላይ በአገርና ህዝብ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን የሚገነዘብ የንግድ ማህበረሰብ መፍጠርምን ይጨምራል። በመሆኑም በ2012 በጀት ዓመት አዳዲስ ሁነቶችን በማካተት ንቅናቄውን በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል። የግብር ንቅናቄው በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ተግቶ የሚሰራና ብልሹ አሰራሮችን የሚጸየፍ ግብር ሰብሳቢ ባለሙያን መፍጠር ላይም አትኩሯል የሚሉት ዳይሬክተሯ በዚህም ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል። ታክስ አገራዊ አጀንዳ እንዲሆንና "ግብር የምከፍለው ለእኔም ለአገሬም ነው" ብሎ የሚያስብ የንግድ ማህበረሰብ፣ ህዝብና ሰራተኛ ለመፍጠር በቀጣይም በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለጹት። ከግብር ከፋዩ ጋር የሚደረጉ ውይይቶችን ጨምሮ ታዋቂ ከያኒያንና ግለሰቦችን በማካተት በ2011 በጀት ዓመት ከነበረው በበለጠ የሚከናወኑ ተግባራትን ያስረዳሉ። ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግብርን በወቅቱ አሳውቀው ለከፈሉ ግብር ከፋዮችና በሥራቸው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የሥራ ክፍሎች እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል። በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፈው ሃምሌ ወር 2011 ዓም ብቻ 18 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ተሰብስቧል ያሉት ወይዘሮ ኢሙ ይህን የሚያህል ገቢ መሰብሰብ የተቻለው ለግብር ከፋዩ እና ለአገልግሎት ሰጪው አካል እውቅና መሰጠቱን ተከትሎ ነው ብለዋል። እንደዳሬክተሯ ገለጻ በዜጎች ዘንድ ግብር መክፈልን በተመለከተ ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ ቢሆንም አገሪቱ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ ማግኘት ያለባትን ገቢ በመሰብሰብ በኩል ግን አሁንም ብዙ መስራት ይጠይቃል። ህብረተሰቡ ግብይት ሲያከናውን ሙሉ ለሙሉ ደረሰኝ አለመጠቀሙን ለአብነት በመጥቀስ ሌሎች በገቢ መሰብሰብ ላይ ያሉ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ወደህጋዊ ስርአት ለማምጣት የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል። በመሆኑም ታክስን አገራዊ አጀንዳ በማድረግ ማህበረሰቡ ግብር መክፈል ለእራሱና ለማህበረሰቡ ግልጋሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት መሆኑን አውቆ ግብርን መክፈል ባህሉ እስኪያደርግ ድረስ ንቅናቄው ይቀጥላል ብለዋል። ሚኒስቴሩ ግብር ከፋዩ በወቅቱ ግብርን አሳውቆ እንዲከፍል ከመስራት ባሻገር የተሻሉ አሰራሮችን መፍጠር፣ አዋጆችና መመሪያዎችንም የማሻሻል ተግባር እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። ለግብር ከፋዩ እንቅፋት የሚሆኑ ሁኔታዎችን ማስወገድ ይቻል ዘንድ ሌሎች አዋጆችና መመሪያዎችም በረቂቅ ደረጃ እየተዘጋጁ ናቸው ብለዋል። የገቢዎች ሚኒስቴር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተለያዩ ግብር ከፋዮች 198 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል።