ቀጥታ፡

በመንግስት ሆስፒታሎች የ'ኤም አር አይ' የምርምራ አገልግሎት ተቋርጧል - ታካሚዎች

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 21/2011 'ኤም አር አይ' የተሰኘውና ነርቭን ጨምሮ አጠቃላይ ውስጣዊ የሰውነት አካልን የጤና ሁኔታ ለመመርመር ዓይነተኛ መጠቆሚያ የሆነው የህክምና መርጃ አገልግሎት በመንግስት ሆስፒታሎች በመቋረጡ 'ለእንግልትና ለከፍተኛ ውጭ እየተዳረግን ነው' ሲሉ ታካሚዎች ገለፁ። 'ኤም አር አይ' (MRI) የአንጎል፣ የደረት፣ የሆድ አካባቢ፣ የህብለሰረሰር፣ በዲስክ መንሸራተት የሚመጣ የአጥንት ችግርን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የጤና እክሎችን በጥልቀት ለመመርመር የሚያስችል የህክምና መርጃ መሳሪያ መሆኑም የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሆኖም በጥቂት የመንግስት ሆስፒታሎች ይሰጥ የነበረው የምርመራ አገልግሎት በመቋረጡ ምርመራው የታዘዘላቸው ህሙማን ለችግር እየተዳረጉ መሆኑን ነው አስተያየት ሰጪዎች ለኢዜአ የገለፁት። በተለይም አገልግሎቱ በአሁኑ ወቅት በመንግስት ሆስፒታሎች አለመኖሩ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደረውን የህብረተሰብ ክፍል ለከፋ ጉዳት እየዳረገ መሆኑንም ታካሚዎች አንስተዋል። በህክምና ምርመራ ሂደት በስፋት የሚፈልገው ይህ መሳሪያ በሚፈለገው መጠን አለመገኘት የህክምና አሰጣጥ ሂደቱንም የተወሳሰበ እያደረገው ነው ሲሉ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ የሚሰጠው በተለይ በአዲስ አበባ ጥቂት የግል ሆስፒታሎችና የህክምና ተቋማት ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ታካሚዎቹ የሚጠየቁት ክፍያም ከአቅማቸው በላይ መሆኑን አመልክተዋል። ለአንድ ጊዜ የኤምአርአይ ምርመራ በግል ሆስፒታሎች የሚጠየቀው ክፍያ ከ3 ሺህ እስከ 4 ሺህ 500 ብር ይደርሳል ሲሉም ተናግረዋል። በገንዘብ እጦት ሳቢያ ምርመራውን ማግኘት ሳይችሉ የሚቀሩት በርካታ መሆናቸውንም ገልፀዋል። በአገሪቱ በርካታ የመንግስት ሆስፒታሎች የማይገኘው የህክምና መሳሪያ 'ኤም አር አይ' መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በአዲስ አበባ የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ  የራዲዮሎጂ የኬዝ ቲም መሪ አቶ እዩኤል በሪሁን ናቸው። ቀደም ሲል በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ብቸኛው የኤምአርአይ መሳሪያ በአሁኑ ወቅት በብልሽት ምክንያት ሥራ ካቆመ አራት ወራት ማለፋቸውንም አቶ እዮኤል ገልፀዋል። በመሆኑም በርካታ ቁጥር ያለውና ምርመራው የታዘዘለት ታካሚ ወረፋ ይዞ የመሳሪያውን ተጠግኖ ለአገልግሎት መብቃት እየጠበቀ ነው ሲሉም አብራርተዋል። ላለፉት አራት አመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ኤምአርአይ ከመበላሸቱ በፊት በቀን ከ45 እስከ 50 ለሚደርሱ ታካሚዎች አገልግሎት ይሰጥ ነበር ብለዋል። ከአገሪቷ በአራቱም አቅጣጫ ለሚመጡ የክልል ታካሚዎች በብቸኝት አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበርም ገልጸዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የጤና ሚኒስቴር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሳህረላህ አብዱላሂ ችግሩ መኖሩን አምነው በዘላቂነት ለመፍታት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል። ቀደም ሲል በከፍተኛ ወጭ የተገዙትና ጥቁር አንበሳን ጨምሮ በተለያዩ ሆስፒታሎች አገልግሎት ይሰጡ የነበሩት መሳሪያዎች ብልሽት ገጥሟቸዋል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታዋ ማሽኖቹን ለመጠገን፣ ብሎም በዘላቂነት ችግሩን ለመፈታት የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ለመግዛት ከአቅራቢ ኩባንያዎች ጋር  ውል መገባቱን ተናግረዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ኤም.አር.አይን ጨምሮ የተለያዩ የምርምራ መሳሪዎችን በክልሎች ጭምር ለማስፋፋት  እየተሰራ መሆኑን ሚኒስቴር ዴኤታዋ ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም