የተመድ ዋና ፀሐፊ የቡድን-7 አባል ሀገራት መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የበለጠ እንዲሰሩ ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የተመድ ዋና ፀሐፊ የቡድን-7 አባል ሀገራት መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የበለጠ እንዲሰሩ ጠየቁ
ኢዜአ ነሃሴ21/2011 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ የቡድን 7 አባል ሀገራት መሪዎች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በሚደረገው ውጊያ ግንባር ቀደም እንዲሆኑ ማሳሰባቸውን ሲጂ ቲ ኤን አፍሪካ ዘገበ። በፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው የቡድን-7 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ጉተሬስ ለአየር ንብረት ሁኔታ መፍትሔ የምንሰጥባቸው መሣሪያዎች አሉን ነገር ግን የፖለቲካ ይሁንታም ጭምር ይፈልጋሉ ማለታቸውን መረጃው አስፍሯል፡፡ የቡድን 7 አባል ሃገራት ጉባኤ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ጠንካራ ተሳትፎ ለመጠየቅ ጥሩ አጋጣሚ እንደነበርም ጉተሬዝ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ የተነሱት አስተያየቶች በመጪው ወር በኒው ዮርክ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የአየር ንብረት የድርድር ስብሰባ ላይ ቅድሚያ እንደሚሰጠውም ዘገባው ያሳያል። የተመድ ዋና ሃላፊ በገለፃቸውም የዓለም ወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥን በመታገል ውስጥ የተጫወቱትን ሚና በማድነቅ ለበለጠ ስኬታማነት የፖለቲካ ይሁንታ ቢታከልበት መልካም ነው ብለዋል፡፡ ጉቴሬስ በማከልም በቅርብ ጊዜ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ (አይፒሲሲ) በተሰጠውን ሳይንሳዊ መረጃ ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል፡፡ እስከ ምዕተ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የሙቀት መጠን ከ 1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ ከፍ እንዳይል ማድረግ ፣ እ.ኤ.አ 2050 ዓለማችን ከካርቦን ልቀት የፀዳች እንድትሆንና እ.ኤ.አ በ 2030 የከባቢ አየር ልቀትን 45 ከመቶ እንቀንሳለን በማለት ተስፋቸውን ተናግረዋል፡፡ የቡድን 7 አባል ሀገራት የብሪታኒያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ጃፓን እና ዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች በፈረንሳይ ባሪትዝ በተካሄደው ጉባኤ እንደተገኙም ዘገባው አትቷል፡፡