ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል ከ647 ሺህ በላይ ለሆኑ ህጻናት የፖሎዮ ክትባት ተሰጠ

ጅግጅጋ (ኢዜአ) ነሀሴ 21 ቀን 2011 በሶማሌ ክልል ለስድስት ቀናት በዘመቻ በተሰጠው የፖሊዮ ክትባት ከ647 ሺህ በላይ ህፃናት መከተባቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡ በክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶችና ሕፃናት ጤና እንክብካቤ ቡድን መሪ አቶ አብዲሸኩር አብዲላሂ ለኢዜአ እንደተናገሩት በክልሉ አምስት ዞኖች ከነሀሴ 11 ቀን 2011 ጀምሮ የፖሊዮ ክትባት በዘመቻ ተሰጥቷል። “ለስድስት ቀናት በተሰጠው ክትባትም ከአምስት ዓመት በታች የሆኑከ647 ሺህ በላይ ሕፃናትን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል” ብለዋል፡፡ በዘመቻው በዶሎ፣ ጀረር፣ ፋፈን፣ ኤረር እና ኖጎብ ዞኖች እንዲሁም በቀብሪያህ፣ ሼድ - ዴር እና አውበሬ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ሕፃናትም መከተባቸውን አቶ አብዲሸኩር ገልጸዋል፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት በተሰጠው በእዚህ ዘመቻ የዓለም ጤና ድርጅት፣ ዩኒሴፍ እና የአሜሪካ በሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ተሳትፈዋል፡፡ በውይይት መድረኩ በመጪው መስከረም ወር ዳግም የሚካሄደውን የፖሊዮ ዘመቻ የተሳካ ለማድረግ የሚያስችሉ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ወክለው ዘመቻውን ሲያስተባበሩ የነበሩት ወይዘሮ ትግስት በላይነህ በበኩላቸው በቅርቡ በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ቦኽ ወረዳ የታየውን የፖሊዮ በሽታ ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዳይዛመት ለመከላከል በዘመቻ ክትባት ተሰጥቷል። ክትባቱ ከአምስት የሶማሌ ክልል ዞኖች በተጨማሪ በጎረቤት ሶማሊላንድና ፑንትላንድ ግዛቶች መሰጠቱንም አመልክተዋል። ቦኽ ወረዳ የታየው የፖሊዮ በሽታ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአምስት ዓመት በኋላ ሲከሰት የመጀመሪያው መሆኑ ተመልክቷል። ኢንስቲትዩቱ ድንበር ዘለል በሽታዎችን ለመከላከል በዘመቻ መልክ ከሚያካሄዳቸው ክትባት በተጨማሪ መደበኛ ክትባት እንዲጠናከርና የህብረተሰቡን ግንዛቤ እንዲያድግ ከክልል ጤና ቢሮዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ ወይዘሮ ትግስት አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም