ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከካሜሮን ጋር ያደረገው ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቀቀ

ነሐሴ 20/2011 የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቶኪዮ ኦሎምፒክ የቅድመ ማጣሪያ የሁለተኛ ዙር ጨዋታውን ከካሜሮን ጋር ተጫውቶ 1 ለ 1 ተለያይቷል። ዛሬ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ለስፔኑ ክለብ ሪያል ቤቲስ የምትጫወተው የአጥቂ መስመር ተጫዋቿ ሚካኤላ አባም በ50ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ግብ ካሜሮንን ቀዳሚ ማድረግ ችላ ነበር። ከእረፍት መልስ ተቀይራ የገባቸው የአዳማ ከተማዋ ተጫዋች ሰናይት ቦጋለ የካሜሮን የተከላካይ ክፍል የሰራውን ስህተት ተጠቅማ በ82ኛው ደቂቃ ያስቆጠረችው ግብ ሉሲዎችን አቻ ማድረግ ችሏል። ኬንያዊቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ናፓኞር አኜታ የካሜሮኗን የተካላካይ መስመር ተጫዋች ሌዩኮ ዩቬኔ በቀይ ካርድ ያሰናበተች ሲሆን ለሁለት የካሜሮን ተጫዋቾች የቢጫ ካርድ አሳይታለች። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመጀሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥርና የግብ እድሎችን በመፍጠር ከተጋጣሚው የተሻለ የነበረ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን የተሻለ እንቅስቃሴ አሳይቷል። በ47 ዓመቱ ካሜሩናዊ አሰልጣኝ አለን ጄዩምፋ የሚመራው የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ ወሳኝ የሚባለውን ግብ ያስቆጠረ ሲሆን ሉሲዎቹ የሜዳ እድላቸውን አለመጠቀማቸው በመልሱ ጨዋታ አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ የቤት ስራቸውን ከባድ ያደርገዋል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የአጥቂ መስመር ክፍል ተቀናጅቶ ከመጫወት እንዲሁም የተገኙትን የግብ እድሎችን ከመጠቀም አንጻር ከፍተኛ ድክመት ታይቶበታል። የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በካሜሮን ርዕሰ መዲ ያውንዴ ይሄዳል። የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በሶስተኛ ዙር ማጣሪያ መስከረም 2012 ዓ.ም ከዴሞክራቲክ ኮንጎና ኢኳቶሪያል ጊኒ አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል። ብሔራዊ ቡድኑ በመጋቢት 2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎን ከዩጋንዳ ጋር አድርጎ በድምር ውጤት 4 ለ 2 ማሸነፉ ይታወሳል። እ.አ.አ በ2020 በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ውድድር የአፍሪካ ዞን የእግር ኳስ የማጣሪያ ውድድር ከመጋቢት 2011 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል። 25 የአፍሪካ አገሮች በማጣሪያው ውድድር ላይ እየተሳተፉ ሲሆን አፍሪካ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ሴቶች እግር ኳስ ያላት የተሳትፎ ኮታ አንድ ብቻ ነው። አምስት ዙር ባለው የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ጨዋታ በመጨረሻው ዙር የሚቀሩ ሁለት ብሔራዊ ቡድኖች በጥር 2012 ዓ.ም በሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ አሸናፊው ቡድን አፍሪካን በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚወክል ይሆናል። ተሸናፊው ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ እና በደቡብ አሜሪካ ዞን (ኮንሜቦል) የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ከቺሊ የኦሎምፒክ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር ጨዋታውን አድርጎ ወደ ቶኪዮ ኦሊምፒክ የማለፍ እድሉን የሚወስን ይሆናል። ከአዘጋጇ ጃፓን ውጪ ብራዚል፣ ኔዘርላንድ፣ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ስዊድንና ኒውዚላንድ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር መሳተፋቸውን ያረጋገጡ የሴት ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው። በቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር የሴቶች እግር ኳስ ውድድር 12 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም