ቀጥታ፡

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ወረዳዎችን ቁጥር 800 ለማድረስ ታቅዷል

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 20/2011 በ2012 በጀት አመት ተጨማሪ 300 ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ ገለፀ። በአዲስ አበባ ከተማም በሁሉም ወረዳዎች አገልግሎቱን ለመስጠት መታቀዱ ተገልጿል። የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት እንደ ሀገር ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰራበት ነው። ጤና መድህን ግለሰቦች አስቀድመው በሚያዋጡት አነስተኛ መዋጮ ራሳቸው አሊያም ቤተሰቦቻቸው የጤና መታወክ ባጋጠማቸው ጊዜ ህክምና የሚያገኙበትና ካልታሰበ የህክምና ወጪ የሚጠበቁበት ስልት ነው። በአሁኑ ወቅት ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አባ ወራና እማ ወራዎች የጤና መድህን አባል ሲሆኑ 20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል። ኤጀንሲው ከአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱና ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ከአዲስ አበባ ከተማ አስሩም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ የኀብረተሰብ ክፍሎች ጋር በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ውይይት አድርጓል። በዚሁ ወቅት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓለሙ አኖ እንዳሉት እስካሁን ባለው ሂደት ከ500 በላይ ወረዳዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን ይህም በሀገሪቷ ካሉ ወረዳዎች ቁጥር አንፃር ሲታይ ከ50 በመቶ በላይ ነው። በተያዘው በጀት ዓመትም አገልግሎቱን በተጨማሪ 300 ወረዳዎች በመጀመር የተጠቃሚዎችን ቁጥር 80 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን ገልፀዋል። አገልግሎቱን እየሰጡ ያሉ ወረዳዎችም አዳዲስ አባሎችን የመመዝገብና ነባር አባሎችም አባልነታቸውን እንዲያድሱ ስራ እንደሚሰራ በማከል። በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎቱን እየሰጡ ካሉ 40 ወረዳዎች በተጨማሪ 76 ወረዳዎች አገልግሎቱን እንዲጀምሩ መታቀዱን የገለፁት ደግሞ የኤጀንሲው የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ አይካ ናቸው። ይህንም ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንና ንቅናቄ መጀመሩን ገልፀው በዚህም በከተማዋ ያሉ ሁሉም ወረዳዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል። አቶ ዓለሙ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ የዛሬውን ጨምሮ እስካሁን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች ውይይት መደረጉን ተናግረዋል። ከሚመለከታቸው አመራሮች ጋርም ተመሳሳይ ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል። በውይይት መድረኮቹ የተገኙ ግብዓቶች በረቂቁ ውስጥ እንደሚካተቱ ገልፀው አዋጁን እስከተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ድረስ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ  ይጠበቃል ብለዋል። የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን "ዘመናዊ እድርና የመደጋገፍ ባህላችን ማሳያ ነው" ያሉት አቶ ዓለሙ፤ በቀጣይም አቅም ለሌላቸው ሰዎች ድጋፍ እያደረጉ ያሉ እድሮችና ሌሎች የማህበረሰብ አባላት ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አገልግሎቱ የሚበረታታና ካለጭንቀት ህክምናን እንዲያገኙ የሚረዳቸው መሆኑን ገልፀዋል። ሆኖም ከግብዓት እጥረትና ከባለሙያዎች ስነ ምግባር ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገባ ተናግረዋል። ውይይት እየተደረገበት ያለው ረቂቅ አዋጅ ሰባት ዋና ዋና ክፍሎችና 32 አንቀፆችን የያዘ መሆኑ ተገልጿል። በውይይቱ ላይ እንደተገለፀው በ2008 ዓ.ም ግለሰቦች 16 ቢሊዮን ብር ለህክምና ሲያወጡ ከዚህ ውስጥ 9 ቢሊዮን ብሩ በራሳቸው አቅም የህክምና ወጪያቸውን የሸፈኑ ሰዎች ያወጡት ነው። ቀሪው 7 ቢሊዮን ብር በሰው ድጋፍ፣ በብድርና ንብረታቸውን ሽጠው የታከሙ ሰዎች ያወጡት የህክምና ወጪ መሆኑን የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም