በሱዳን የሽግግር መንግስት ለመመስረት የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በሱዳን የሽግግር መንግስት ለመመስረት የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው ተባለ
ነሐሴ 20/2011 የሱዳን ህዝብና መንግስት ያጋጠማቸው ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚና መጫወቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የመንግስት ምስረታው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው ብሏል። የሱዳን ተቃዋሚዎችና ወታደራዊ ኃይሉ በኢትዮጵያ አደራዳሪነት ከቀናት በፊት የሽግግር መንግስት ለመመስረት መስማማታቸው ይታወሳል። ይህ የጣምራ የሽግግር መንግስት ሱዳንን የሶስት ዓመታት የሚያስተዳድር ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው። በሱዳን የተከሰተው ችግር የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ከሌሎች አጋሮቿ ጋር በመሆን ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ስትጫወት ነበር ብለዋል። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ አገሪቷ አቅንተው በተለያየ ጎራ የሚገኙ አካላትን ማነጋገራቸውንም በማመልከት። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሱዳን ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ ልዩ ልዑክ መሰየማቸውንም ነው አቶ ነብያት ያመለከቱት። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን በመወከል አደራዳሪ የነበሩት አምባሳደር መሐሙድ ድሪር እና በካርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሃላፊነት ወስደው የቅርብ ክትትል ሲያደርጉ እንደነበር ገልጸዋል። በዚህም ሁለቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች የሰላም ስምምነት በመፈረም የጋራ የሽግግር መንግስት ለመመስረት መስማማታቸው ለኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ። ኢትዮጵያ ለአገሪቱ ሰላም መረጋገጥ የተጫወተችው ሚናም ከሱዳን ህዝብ ባለፈ በሌሎች ዘንድ ልዩ አድናቆት የተቻረው መሆኑን ነው የተናገሩት። ኢትዮጵያ በቅርቡ ከተከሰተው የሱዳን ችግር ባለፈ ለሶማሊያና ለደቡብ ሱዳን ሰላም መረጋገጥ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች። ከስድስት ዓመታት በፊት የተቀሰቀሰውና ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች የሞቱበትና ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ የተሰደዱበትን የደቡብ ሱዳን ግጭት ለማስቆም ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ጋር የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች ትገኛለች። የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስምምነት ላይ በመድረስ የሽግግር መንግስት እንዲመሰርቱ የወቅቱ የኢጋድ ሊቀ-መንበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው ስብሰባ ላይ አሳስበዋል።