ቀጥታ፡

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ መንገዶች በመበላሸታቸው በእንቅስቃሴያችን ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል- ነዋሪዎች

ነቀምቴ ነሐሴ 20  ቀን 2011 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ በሁለት አቅጣጫዎች የተሰሩ መንገዶች በመበላሸታቸው በእንቅስቃሴያቸው ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩን ነዋሪዎች ገለጹ። ከነዋሪዎቹ አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስረዱት ከሻምቡ--አጋምሳ 96 ኪሎ ሜትርና ከማዞራ - ፍንጯአ ስኳር ፋብሪካ 33 ኪሎ ሜትር የሚወስዱት መንገዶች በመበላሸታቸው ለችግር ተዳርገዋል። ከአስተያየት አቅራቢዎቹ በጃርቴ ጃርደጋ ወረዳ የአሊቦ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደሳለኝ ገመዳ ኅብረተሰቡ በመንገድ ብልሽትና መደርመስ ምክንያት አገልግሎት በማጣት እየተቸገረ ነው ይላሉ። በዚህም ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብና አቅመ ደካሞች፣እናቶችና ሕፃናት የሕክምና አገልግሎት ማጣት እየገጠማቸው መሆኑን በማስረጃነት ያቀርባሉ። ወደ ዞኑ የሚወስደው መንገድ ጫብር፣ሹሉከ እና መልካ በሎ በሚባሉ ቦታዎች በመደርመሱ 27 ብር የነበረው የትራንስፖርት ታሪፍ ከ150 ብር እስከ 200 ብር በመድረሱ ኅብረተሰቡ ላልተፈለገ ወጪ እየተዳረገ መሆኑን ተናግረዋል። የዚሁ ቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ አበሩ ጉያሳ በበኩላቸውየመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት በመቋረጡ ለችግር መጋለጣቸውን አስረድተዋል። በዞኑ የአሙሩ ወረዳ የአጋምሳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጎቦሾ ሁንዴ ሶስት ወረዳዎችን የሚያገናኘው የአጋምሳ-ሻምቡ  መንገድ በመዘጋቱ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ ከዞኑ ርዕሰ ከተማ ማግኘት ያለበትን አገልግሎት እንደማያገኝም አስታውቀዋል። የሆሮ ቡሉቅ ወረዳ የሰቀላ 01 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መሰረት ቶጵያ ከክረምቱ ዝናብ ጋር ተያይዞ በተከሰተው የመሬት መደርመስ ሳቢያ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘትና ነፍሰ ጡር እናቶች ክትትል ለማድረግ  መቸገራቸውን ተናግረዋል። እህል አስፈጭቶ ለመጠቀም ባለመቻላቸው በባህላዊ ወፍጮ ለመጠቀም  ተገደናል ብለዋል። የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ ቦደና ረጋሳ ተጠይቀው ነዋሪዎቹ ያነሱት ቅሬታ ትክክለኛና መፍትሔ እየተፈለገለት መሆኑን ይገልጻሉ። መንገዶቹ ኦሮሚያን ከአማራ ክልሎች፣ሆሮ ጉድሩ ወለጋንና ከምሥራቅ ወለጋ ዞኖችና የዞኑን አራት ወረዳዎችን ስለሚያገናኙ የሚያስከትሉት ሁለንተናዊ ጉዳት ቀላል ያለመሆኑንም ያምናሉ። ቸግሩን  ለመፍታት  ግንባታቸውን ካከናወነው ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር መፍትሄ እያፈላለጉ መሆናቸውን አመልክተዋል። በዚህም  የኢትዮጵያ፣የኦሮሚያና የዞኑ መንገዶች ባለሥልጣናት በመቀናጀት ችግሩን ለማቃለል ይሰራሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም