ቀጥታ፡

ውኃና ተለዋዋጭ የአየር ጸባይ ስጋት

ውኃና ተለዋዋጭ የአየር ጸባይ ስጋት በአዋሽ ተፋሰስ የተደረገ ጥናት ባለፈው ሐምሌ ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 350 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል የአየር ጸባይ ለውጥን በመመከት ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች። አገራዊ የችግኝ ተከላውም በመላው የአገሪቷ ክፍል 4 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ትናንት በይፋ መጠናቀቁ ይታወሳል። ኢትዮጵያ የተቀናጀ የግብርና ስርአትን ባለመከተሏ በየአመቱ ለእርሻ የሚሆን ቦታ ፍለጋ ያለአግባብ ደኖቿን ትጨፈጭፋለች፤ ልቅ ግጦሽም ስውሩ የውድመት መሳሪያ ነው። እነዚህ ጫናዎች ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተደማምረው የአገሪቷን የተፈጥሮ ሃበት አጠቃቀም ልጓም እንዲበጅለት እያሳሰቡ መሆናቸውን በእንግሊዝ አለም አቀፍ የልማት ተቋም የገንዘብ ድጋፍ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተሰራ ጥናትን በመጥቀስ ለንደን የሚታተመው ዘ ኮንቨርሴሽን ድረ-ገጽና ሌሎች በሳይንስ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ድረ-ገጾች ዘግበውታል። በአየር ጸባይ ለውጥ የተነሳ የውኃ ሃብቱ እየሳሳ ሲመጣ የመሬት መሸርሸሩ አስከፊ ደረጃ ላይ ይደርሳል። ነገር ግን የአየር ጸባይ ለውጥ በውኃ ሃብቱ ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ በተመለከተ ሳይንስ ምን ይነግረናል? እንዲሁም በኢትዮጵያ ስላለው ኢኮኖሚና ስለ ህዝቦቿስ ምን ይነግረናል ? እ.አ.አ ከ 2015 አንስቶ ሪች የተሰኘ አለም አቀፍ የምርምር ፕሮግራም የድሆችን የውኃ ዋስትና ለማረጋገጥ ሲሰራ ቆይቷል። ለዚህ ጥያቄያችንም መልስ ሊሰጠን ይሞክራል። ፕሮግራሙ ትኩረቱን ያደረገው በአገሪቷ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወት ትልቅ ጠቀሜታ ባለው በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ነው። ተፋሰሱ በአገሪቷ ካለው የመሬት ሃብት 10 በመቶ፡ ከህዝብ ብዛቱ 17 በመቶ የሚወክል ነው። የአገሪቷ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቷ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚናም ይጫወታል። በኢትዮጵያ የአየር ጸባይ ለውጥን ተከትሎ በሚፈጠሩ የውኃ እጥረቶች ላይ በአብዛኛው ጥናት የተሰራው በናይል ተፋሰስ አካባቢ ነው። ቀጣይ ፕሮጀክቶችን መሰረት ያደረጉ ጥናቶችን ለመስራት አካባቢዎቹ የተለያዩና ልል በመሆናቸው በሁሉም ቦታ ሊተገበሩ አይችሉም። ይህ ጥናት በተለየ ሁኔታ በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢ በአየር ጸባይ ለውጥ የተነሳ የሚፈጠረውን የውኃ አጥረት በዝርዝር የሚያሳይ ነው። ጥናቱ የተከናወነው የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት አድርጎ መሆኑም ተገልጿል። የጥናቱ ግኝት እንደሚያሳየው አካባቢው በቀጣይ ጊዜያት ሞቃት፣ ደረቃማና ከፍ ያለ የውኃ አጥረት ይከሰትበታል። ይህ ደግሞ በኢኮኖሚውና በሰብዓዊ ልማቱ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ይህንኑ ጉዳት ለመቀነስ የሚረዳ ለአየር ጸባይ ለውጥ የማይበገር ፖሊሲን አስፈላጊነት ይጠቁማል። ውኃ ለህዝቡና ለኢኮኖሚው ወሳኝ ነው በኢትዮጵያ የዝናብ ስርጭትና የውኃ ሃብቱ ተደራሽነት በእጅጉ ተለዋዋጭ ነው። የውኃ እጥረት ደግሞ በአብዛኛው ማህበረሰቦችን፣ ኢንዱስትሪውንና በተለይ ደግሞ ግብርናውን በእጅጉ ይጎዳዋል። በኢትዮጵያ ሁሉም የእህል ዘሮችና የኢንዱስትሪ ግብአት የሆኑ እህሎች በዝናብ ላይ ጥገኛ በሆነ ግብርና የሚበቅሉ ናቸው። በአገሪቷ የውጭ ግብይት የኢንዱስትሪ እህሎች 85 በመቶ ድርሻን እንደሚይዙም ጥናቱ አመላክቷል። ከዚህ በተጨማሪ የአገሪቷ የኤሌክትሪክ ኃብት በውኃ ላይ ጥገኛ ሲሆን 90 በመቶ የሚጠጋው የኃይል አቅርቦት ከውሃ ይገኛል። ይህ በውኃ ላይ ጥገኛ የሆነው የአገሪቷ ኢኮኖሚ ኢትዮጵያ ከውኃ ጋር ተያይዞ ለሚከሰት የአየር ጸባይ ለውጥ በእጅጉ ተጠቂ መሆኗን ያሳየናል። እነዚህም የውኃ እጥረትን፣ ድርቅንና ጎርፍን ያጠቃልላሉ። የ 5 በመቶ የዝናብ እጥረት በግብርና ውጤታማነት ላይ የ 10 በመቶ ቅናሽ የሚያመጣ ሲሆን የአገሪቱን አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት እድገት ደግሞ በ 5 በመቶ ወደ ኋላ ይጎትተዋልም ተብሏል። የአዋሽ ተፋሰስ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለጥቃት ተጋላጭ መሆኑም ይታወቃል። አካባቢው በተደጋጋሚ በድርቅና በጎርፍ አደጋ ይጠቃል። በአካባቢው ያለው የውኃ አቅርቦትም በመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ የሚወሰን ሲሆን በታችኛው የተፋሰሱ አካባቢ የዝናብና የከርሰ ምድር ውኃ አጥረቱ የጎላ ነው። በከፍተኛ ቦታዎች ላይ ደግሞ በርከት ብሎ ይታያል። የአየር ጸባይ ለውጡ ሁኔታውን በምን ደረጃ ሊያባብሰው ይችላል? ሞቃታማና ደረቅ የሆነው መጻኢ ጊዜ፡ ተፋሰሱን መሰረት ያደረገውን ሞዴል መሰረት በማድረግ የተሰራው ጥናት በአካባቢው የሙቀትና የእርጥበት መጠኑ ለውጥ እንዳለው ያሳያል። ተመራማሪዎቹ ለውጡን ከቀደመ ታሪክ ጋር በማነጻጸር በሰሩት ጥናት በመጪው ጊዜ በአካባቢው ያለው የውኃ እጥረት እንደሚባባስ አረጋግጠዋል። በዚህም እስከ ክፍለ ዘመኑ ማብቂያ የውኃ እጥረቱ እየጨመረ እንደሚሄድም አስታውቀዋል። የጥናቱ ግኝት እንደሚያመለከተው የመስኖ ወቅት በሚባሉት ሚያዚያ፣ግንቦትና ሰኔ እጥረቱ እንደሚብስም ጠቁመዋል። በነዚህ ወራት እርጥበቱ በመቀነስና ሙቀቱ ደግሞ በመጨመር የውኃ ሃብቱን ያሳንሰዋል። በአገሪቷ ለሚገኙና አነስተኛ ማሳ ላላቸው ገበሬዎችና ለሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ወቅቱ በዋናነት የመስኖ እርሻ የሚከናወንበት ነው። በተጨማሪም ለመስኖና ለኃይል ማመንጫ የሚያስፈልገውን ውኃ በመሻማት ግጭት ሊከሰት ይችላል ተብሎም ይገመታል። ችግሩ እየጎላ ሲሄድ ለሰብአዊ ፍጡር የሚያስፈልገው የውኃ ሃብት ይጠፋና ፈተናውን ያበዛዋል። የመጠጥ ውኃ፣የጤና መጠበቂያና ለንጽህና የሚሆን ውኃ ማግኘትም ፈተና ይሆናል። ይህ ደግሞ በተለይ ድሆችንና በተፋሰሱ ግርጌ የሚኖሩ ሰዎቸን የበለጠ ያጠቃቸዋል። ለአየር ጸባይ የማይበገር ፖሊሲ ለአየር ጸባይ የማይበገር ፖሊሲ ማውጣት የውኃ ሃብት አጠቃቀምና ተደራሽነት እንዲሁም በመቀነስ ላይ የሚገኘውን ሃብት ለማስተካከል ወሳኝ ነው። በዚህ ላይ የአየር ጸባይን የተመለከቱ መረጃዎችን በማከለ ሁኔታ መጠቀም በራሱ የአመራሩን ውሳኔ የሚፈልግና ፈተና እንደሆነም ተመራማሪዎቹ ይጠቅሳሉ። ይህ ደግሞ ሳይንሳዊ መረጃን የሚሻ ከመሆኑ በላይ የአሁኑንና የመጪውን ጊዜ የውሃና አየር ጸባይ ነባራዊ ሁኔታ መረዳትን ይጠይቃል። ተመራማሪዎቹ የተሻለ የውኃ አስተዳደርንና አጠቃቀም ፖሊሲን ለመደገፍ ይረዳሉ ያሏቸውን የጥናት ግኝቶቻቸውንም እንደሚከተለው አስቀምጠዋል፡ •የአየር ጸባይን የተመለከቱ መረጃዎችን ተደራሽነት ማሳደግ እንዲሁም በመንግስታዊና ተመሳሳይ ተግባር በሚያከናውኑ ተቋማት የሚገኙ ባለሙያዎችን የውኃ አስተዳደር አቅም መገንባት፤ •ተጨማሪ የውኃ ሃብቶችን ማበልጸግ ለምሳሌ የጉድጓድ ውኃን ለመደገፍ የሚረዳውን የከርሰ ምድር ውኃ ሃብትን ማበልጸግ፤ •በእጅጉ ተጠቂ የሆኑትን የተፋሰሱ አካካባቢዎች ዝቅተኛ የሀብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ ልማት ማከናወን። በእርግጥ ለወደፊቱ ደረቃማ ቦታዎችን መሰረት አድርጎ ምን ያህል የውኃ ሃብት ይከፋፈል? የሚለው የፖለቲካ ውሳኔን የሚፈለግ ፈታኝ ተግባር መሆኑ አይካድም። ተግባሩ ውጤታማ የአስተዳደር ስትራቴጂ የሚጠይቅና፣ ቀናኢ የፖለቲካ ውሳኔና ኢንቨሰትመንትን የሚፈልግም ነው። ባለድርሻ አካላትንም በማሳተፍ እገዛቸውን ማግኘት ግድ ይላል። ሳይንቲስቶችም ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር በቅርበት መስራት ይጠበቅባቸዋል። አለም አቀፉን የአየር ጸባይ ለውጥ ለመታገል ኢትዮጵያ የጀመረቸው የአረንጓዴ ልማት ግስጋሴ ተስፋ ሰጪ በመሆኑም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያግዛት ግድ ይለዋል። ዛፎች የተቃጠለ አየርን ለማስወገድ የሚጫወቱት ሚና ላቅ ያለ በመሆኑ እስኪጸድቁ መንከባከብም የህብረተሰቡ ግዴታ ነው። ዛፎች መተከላቸው ብቻውን አካባቢያዊ የአየር ጸባይ ለውጥ መከላከልን ለማበልጸግና የመሬት መሸርሸርን ለመከላከል በቂ ነውን? መልሱ አስቸጋሪ ቢሆንም ሙቀት፣ የመሬት መድረቅና የውኃ ረሃብ ለገጠማት አገር ለአየር ጸባይ የማይበገር ፖሊሲን በሳይንስ ተደግፎ ማውጣት ጊዜ የማይሰጠው ግዴታ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም