ሲሸልስ በባህር ትራንስፖርት መስክ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት መስራት እንደምትፈልግ ተገለጸ

92
አዲስ አበባ  ነሀሴ 17 /2011 ሲሸልስ በባህር ትራንስፖርት መስክ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት መስራት እንደምትፈልግ የሲሸልስ ምክትል ፕሬዚዳንት ቪንሰንት ሜሪቶን ተናገሩ። በኬንያ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ለሲሸልስ ፕሬዚዳንት የሹመት ደብዳቤያቸውን ካቀረቡ በኋላ ከአገሪቷ ምክትል ፕሬዚዳንት ቪንሰንት ሜሪቶንና ከውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ዴኤታው አምባሳደር ባሪ ፎኽ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለኢዜአ በላከው መረጃ አመላክቷል። አምባሳደሩ ከቱሪዝም፣ የሲቪል አቪዬሽን፣ የወደብና የውሃ አካላት ሚኒስትር ከሆኑት ከዲዲየር ዶግሊይ ጋርም መወያየታቸው ተጠቅሷል። በውይይቱም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ቪንሰንት ሜሪቶን ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ላይ እያበረከተች ያለችውን አስተዋፅኦ አድንቀው፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል። በተለይም በባህር ላይ ትራንስፖርት መስክ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት መስራት እንደምትፈልግና ለዚህም ከፍተኛ ዝግጁነት እንዳላት ገልጸዋል። አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው ሲሸልስ የኢትዮጵያ ጠንካራ ወዳጅ መሆኗን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያም ከሲሸልስ ጋር በቱሪዝም፣ በንግድና በኢንቨስትመንት መስኮች መተሳሰር እንደምትፈልግ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጀመረውን ትስስርም በሰላም፣ በብልጽግናና ቀጠናዊ ውህደት እንዲመጣ በባህር ትራንስፖርት መስክ ላይ ለመድገም የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል አምባሳደሩ። አምባሳደሩ ከሲሸልስ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ዴኤታ አምባሳደር ባሪ ፎኽ ጋር ባደረጉት ውይይትም በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተዘጋጁ የመግባቢያ ሰነዶች በፍጥነት ተጠናቀው ለስምምነት እንዲቀርቡ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መምከራቸውም ተገልጿል። በውይይቱም የአገራቱ የጋራ የሚኒስትሮች መድረክ በቅርብ ጊዜ እንዲደረግ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ከሲሼልስ የቱሪዝም፣ ሲቪል አቪዬሽን፣ የወደብና የውሃ አካላት ሚኒስትር ከሆኑት ዲዲየር ዶግሊይ ጋር ባደረጉት ውይይትም ኢትዮጵያና ሲሸልስ ‘የጋራ የእረፍት ጊዜ መዳረሻ’ በሚል የጀመሩትን የጋራ የቱሪዝም ፕሮጀክት እውን ለማድረግ መስራት እንደሚገባቸው ተነጋግረዋል። ሲሸልስ በቱሪዝም መስክ ያላትን የላቀ ተሞክሮ በደቡብ-ደቡብ ትብብር ማዕቀፍ ስር ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ እንደሆነችም ተገልጿል። በናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከኬንያ በተጨማሪ ማላዊ፣ ሲሸልስና ኮሞሮስን ሸፍኖ እንደሚሰራ ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም