የአሸንዳ በዓልን ለዓለም ማህበረሰብ የማስተዋወቁ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል....የውጭ አገር ቱሪስቶች - ኢዜአ አማርኛ
የአሸንዳ በዓልን ለዓለም ማህበረሰብ የማስተዋወቁ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል....የውጭ አገር ቱሪስቶች

ማይጨው (ኢዜአ) ነሀሴ17 / 2011 የአሸንዳ በዓል በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ እንዲታወቅ የማስተዋወቁ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በመቀሌ የአሸንዳ በዓል ላይ የታደሙ የተለያዩ የውጭ አገር ቱሪስቶች ተናገሩ። ከትናንት ጀምሮ እየተከበረ ባለው የአሸንዳ በዓል ላይ ልጃገረዶች በባህላዊ ልብስ ተውበው፣በልዩ ልዩ ጌጣጌጦች አሸብርቀውና በተለያዩ የጸጉር አሰራር ደምቀው በዓሉን አድምቀውታል። እየተከበረ ባለው በዓል ላይ ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገር የመጡ ጉብኚዎች የበዓሉ ታዳሚዎች ሆነዋል። ከውጭ አገር የመጡትና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ቱሪስቶች እንዳሉት የአሸንዳ በዓል የዓለም ማህበረሰብ በሚገባ እንዲያውቀውና ለቱሪዝም ልማት ተጨማሪ ገቢ እንዲያስገኝ የማስተዋወቁ ስራ ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ ለሰባት ጊዜ ወደኢትዮጵያ እንደመጣና በአሽንዳ በዓል ላይ ለአራት ጊዜ መታደሙን የገለጸው የቤልጂየም ተወላጅ አንድሬ ክርስሜ፣ በበዓሉ ላይ የሚሳተፉ ልጃገረዶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመምጣቱ ማየቱን ተናግሯል። "ከአራት ዓመት በፊት ሴቶች በቡድን ሆነው ከመጨፈር ባለፈ እንደዚህ በብዛት ሆነው ሲያከብሩ አላየሁም፣ አሁን ግን ለበዓሉ ትኩረት ተሰጥቶት በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ነው" ብሏል። በዓሉ የዓለም ማህበረሰብ እንዲያውቀው ከማድረግ አንፃር በቀጣይ ብዙ ሥራ መሰራት እንዳለበትም አመልክቷል። "ድንቅ የሆነ ባህል ነው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ እንደ እኔ ብዙ ቱሪስት ወደእዚህ ይመጡ ነበር" ብሏል። "ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የመጣሁት፤ በዚህ ውብ በሆነ የአሸንዳ በዓል ላይ በመካፈሌ በጣም ደስ ብሎኛል" ያለችው ደግሞ ከስፔን ባርሴሎና ከተማ የመጣችው ኤዳ ሙንታዳስ ናት። ሰለ አሽንዳ በዓል ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት መረጃ እንዳልነበራት የተናገረችው ኤዳ፣ አሸንዳ ሴቶች አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን በነጻነት የሚገልፁበት ታላቅ በዓል መሆኑን መረዳቷን ገልጻለች። ከኢትዮጵያ ውጪ ያለው ህብረተሰብ እንዲያውቀው በዓሉን የማስተዋወቅ ሥራ በቀጣይ ሊተኮርበት እንደሚገባ ነው የገለፀችው። ከባርሤሎና ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ መጥቶ በአሸንዳ በዓል ላይ የተካፈለው ፌራን ሞራ በበኩሉ፣ በመጣበት አካባቢ ሴቶች ለብቻቸው የሚያከብሩት በዓል መኖሩን ተናግሯል። በአሸንዳ በዓል ልጃገረዶች የለበሱት ልብስና የፀጉራቸው አሰራር ተመሳሳይ መሆኑ በዓሉ የተለየና በጣም ማራኪ እንዲሆን አድርጓታል በማለት ስሜቱን ገልጿል። “ይህን ውብ ባህል በተለያየ መንገድ በማስተዋወቅ የዓለም ማህበረሰብ እንዲያውቀው ማድረግ ይገባል” ሲልም ተናግሯል። በዓሉ "የሴቶችና የልጃገረዶች ጨዋታ" ተብሎ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን መገለጹ ይታወቃል።