ቀጥታ፡

የአየርላንድ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የልማት ትብብር የሚያጠናክር ስትራቴጂ በማዘጋጀት ላይ ነው

ነሀሴ17/2011የአየርላንድ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የልማት ትብብር ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን መንገድ የሚጠቁም ስትራቴጂ በማዘጋጀት ምእራፍ ላይ መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር አስታወቁ። ኢዜአ ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ ተሰናባቿ የአየርላንድ አምባሳደር ሶንያ ሃይላንድ መንግስታቸው ባለፉት ስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ለኢትዮጵያ ልዩ ልዩ የልማት ውጥኖች ማስፈፀሚያ የሚሆን የ160 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ መስጠቱን አመልክተዋል። የልማት ድጋፉ በጤና አገልግሎት፣ በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በማህበራዊ ዋስትና፣ የአደጋ ተጋላጭነት መከላከልና በሰብአዊ እርዳታ ዘርፎች ነው። በአየርላንድ መንግስት ድጋፍ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚካሄዱት የልማት መርሃ ግብሮች ሁሉ የኢትዮጵያው በትልቅነቱ ይጠቀሳል። በመጪዎቹ ዓመታትም ይኸው የልማት ትብብር ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን መንገድ የሚጠቁም ስትራቴጂ በመዘጋጀት ሂደት ላይ መሆኑን አምባሳደሯ ጠቅሰዋል። ቀጣዩ የሁለቱ አገሮች የትብብር ግንኙነት በምጣኔ ኃብታዊ ልማትና በፖለቲካ የለውጥ ተግባራት እንደዚሁም በኢትዮጵያ ለሰብአዊ እርዳታ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን መቀነስ በሚቻልባቸው መስኮች ላይ የሚያተኩር እንደሚሆን አምባሳደር ሃይላንድ ተናግረዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ የአየርላንድ ልኡካን ቡድኖች በኢትዮጵያ ያካሄዳቸው የሥራ ጉብኝቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ በርካታ መሆኑን ጠቅሰው፤ ''ይህም አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር  የትብብር ግንኙነቷን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል'' ብለዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ገዥ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። በኢትዮጵያና አየርላንድ መካከል ያለው የልማት ትብብር ከ25 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የአገሮቹን የፖለቲካና ምጣኔ ኃብታዊ ግንኙነት በማሳደግ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በዶክተር አብይ አህመድ በሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ከዓመት በፊት የተጀመረው የምጣኔ ኃብታዊና ፖለቲካ ለውጥ ሂደት ይሳካ ዘንድ የአየርላንድ መንግስት የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ''የአየርላንድ መንግስት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ጋር በቅርቡ የፈረመው የትብብር ስምምነት መንግስታቸው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ለውጥ ሂደት ለማገዝ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል'' ብለዋል። በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታን በማረጋገጥ ረገድ የኢትዮጵያ ሚና ቁልፍ መሆኑን የሚገነዘበው የአየርላንድ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተቀራርቦ መስራቱን እንደሚቀጥል አስረድተዋል። የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ወሳኝ መሆኑን የገለፁት ተሰናባቿ አምባሳደር፤ ''የሚፈለገው ውጤት ይመጣ ዘንድ የኢትዮጵያ ጥረት በእጅጉ አስፈላጊ ነው'' ብለዋል። ኢትዮጵያ ከሁለት አስርታት በላይ የቆየውን የኤርትራ ችግር በሰላም ለመፍታት የወሰደችውን እርምጃ እንዲሁም በጎረቤት ሱዳን የፖለቲካ እርቅ እንዲወርድ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያከናወነችውን ተግባር አምባሳደሯ አድንቀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም