ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች- አሎክ ሸርማን

75
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 17/2011 ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የልማት ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የአገሪቱ ዓለም ዓቀፍ ልማት ትብብር ሚኒስትር አሎክ ሸርማን ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የብሪታኒያ ዓለማቀፍ ልማት ትብብር ሚኒስትር አሎክ ሸርማንን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። የሁለቱ ባለስልጣናት ውይይት በዋናነት ያተኮረው የአገሮቹ ትብብር በሚጠናከርበት መንገድ ላይ ነው። በዚሁ ወቅትም የዓለማቀፍ ልማት ትብብር ሚኒስትሩ እንዳሉት ብሪታኒያ ካሏት ጠንካራ ወዳጆች  መካከል ኢትዮጵያ አንደኛዋ ናት። ብሪታኒያ እርሳቸው በሚመሩት ተቋም አማካኝነት ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ከምታደርገው ድጋፍ መካካል ትልቁን ድርሻ የሚወስደው በኢትዮጵያ የምታከናውነው መሆኑንም አብራርተዋል። "በቀጣይም ይህን ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን " ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የብሪታኒያ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርቦ በመስራት በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የተጀመረው የምጣኔ ኃብት ለውጥ ይሳካ ዘንድ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ቆይታም ይህ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል መስማማታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል። ብሪታኒያ የኢትዮጵያን የታክስ አሰባሰብ ስርዓትን ለማሻሻል የሚያግዝ መርሃ ግብር ከአንድ ዓመት በፊት በይፋ ጀምራለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም