የአሸንዳ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓልን ለትውልድ ለማስተላለፍ ሃላፊነታችንን መወጣት አለብን - ወይዘሮ ዳግማዊት - ኢዜአ አማርኛ
የአሸንዳ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓልን ለትውልድ ለማስተላለፍ ሃላፊነታችንን መወጣት አለብን - ወይዘሮ ዳግማዊት
የአሸንዳ፣ አሸንድዬና ሶለል በአል ሴቶች ከጓዳ ወደ አደባባይ ወጥተው የሚያከብሩት የሴቷ የነጻነት ቀን ማሳያ በዓል በመሆኑ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሃላፊነታችንን መወጣት አለብን ሲሉ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ። በዓሉን ዛሬ በየካ ክፍለ ከተማ የአማራ ሴቶች ማህበር ከአማራ ክልል ተወላጆችና ከሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በመሆን በድምቀት አክብረዋል። በበአሉ ላይ የታደሙት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት በዓሉን ለማስተዋወቅ ትኩረት ተሰጥቶ በአስሩም ክፍለ ከተሞች እንዲከበር መደረጉን ገልፀዋል። ''ባህሉን ለማበልፀግ በየአመቱ ከፍ ባለ ደረጃ በማክበር ለትዉልድ የማስተላለፍ ሃላፊነታችን መወጣት አለብን'' ብለዋል። አሸንዳ፣ አሸንድዬና ሶለል በአማራ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ሴቶች ከጓዳ ወጥተው በነፃነት አደባባይ ላይ የተለያዩ ጣዕመ ዜማና ዉዝዋዜን የሚያሳዩበት ባህል በመሆኑ የሴቶች የነፃነት ቀን እንደሆነ ተናግረዋል። ወይዘሮ ዳግማዊት በዓሉ ታሪካዊና ኃይማኖታዊ ይዘት ያለዉ ታላቅ ባህል መሆኑን ገልጸው፤ ልጃገረዶች፣ እናቶችና ህፃነት ያለ ልዩነት የሚሳተፉበት ነባር ባህል መሆኑን አስታውሰዋል። በየካ ክፍለ ከተማ የአማራ ሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ወይኒቱ ወንዲራድ በበኩላቸው የአሸንዳ፣ አሸንድዬና ሶለል በአል በአዲስ አበባ ከተማ መከበሩ በመዲናዋ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ባህላቸዉን ለሌሎች ማስተዋወቅ የሚችሉበትን ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል። የአማራ ክልል ባህሎች ጎልተዉ እንዲወጡና እንዲታወቁ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ወይኒቱ፤ አሸንዳ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓል በአዲስ አበባ መከበሩ ባህሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።