ከአባላት የሚሰበሰብ ሀብት በማሳደግ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው-ማህበሩ - ኢዜአ አማርኛ
ከአባላት የሚሰበሰብ ሀብት በማሳደግ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው-ማህበሩ
ሀዋሳ ነሐሴ 16 / 2011 ከአባላት የሚሰበስበውን ሀብት በማሳደግ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ችግር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስታወቀ። የማህበሩ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤት ሠራተኞች ጋር ዓመታዊ የምክክር መድረክ አካሂዷል ፡፡ የማህበሩ ዋና ፀሐፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ በወቅቱ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። "በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር ከ8 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ደርሷል"ያሉት ዋና ፀሐፊው፣ ለዜጎቹ አፋጣኝ ድጋፍ ለማድረግ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል ። "ማህበሩ ካሉት 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን አባላት የሚሰበስበው ሀብት ድጋፉ ከሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር አንጻር ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር ሀብት የማሰባሰቡ ሥራም በአግባቡ እየተከናወነ ባለመሆኑ የዜጎችን ችግር ትርጉም ባለው በመልኩ ለመፍታት አልተቻለም" ብለዋል ። ከውጭ ለጋሾች የሚገኘው ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱ ደግሞ ተጨማሪ ሥጋት መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ "የዜጎችን ችግር ትርጉም ባለው መልኩ ለመፍታት በአገር ውስጥ የሚመነጭ ሀብትን በአግባቡ ማሰባሰብና መጠቀም ይገባል" ያሉት ዶክተር መሸሻ፣ ማህበሩ ያሉበትን ክፍተቶች ለመሙላት ተጨማሪ 5 ሚሊዮን አባላትን ለማፍራት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል ። በከተማ ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ የአባላት ምልመላ እየተካሄደ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል ። አባላትን፣ የገንዘብ ተቋማትን፣ ማህበራትን፣ ኮንፌዴሬሽኖችንና ሌሎች ተቋማትን በማስተባበር በሚሰበሰብ ገቢም ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ችግር የሚፈታበት አቅም መኖሩንም ጠቁመዋል ፡፡ ማህበሩ በብሔራዊ ጽህፈት ቤት ደረጃ የሰብዓዊ ድጋፍ ፈንድ በማቋቋም ባለፉት ሶስት ሳምንታት 16 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከአገር ውስጥ ማሰባሰቡንም ገልጸዋል ። ማህበሩ ዕቅዱን ለማሳካት በአግባቡ ለማስተባበርና ከላይ እስከታች ካሉት መዋቅሮች ጋር ሥርዓት ባለው መልኩ መቀናጀት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል ። በማህበሩ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ታከለ ከ2010 በጀት ዓመት ጀምሮ በክልሉ በርካታ ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች መከሰታቸውን ተናግረዋል። "የቅርንጫፉን ሠራተኞችና የክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶችን በማስተባበር ለተጎዱ ዜጎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ተደርጓል" ብለዋል ። አሁን ላይ እያጋጠሙ ካሉ አደጋዎች አንፃር ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች አፋጣኝ ድጋፍ ለማድረግ እየከበደ በመምጣቱ በገንዘብም ሆነ በዕውቀታቸው ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ የሚችሉ የሴክተር መስሪያ ቤት ሠራተኞችን ተሳትፎ ለማሳደግና በተደራጀ መልኩ ለመምራት መድረኩ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል ። በክልሉ በየደረጃው ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ማስተባበር ከተቻለና በተደራጀ መልኩ ከተመራ ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት እንደሚቻል አመልክተዋል ። የኅብረተሰቡን የአደጋ ተጋላጭነት አስቀድሞ በመከላከል ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔዎችን ማበጀት እንደሚገባ የገለፁት ኃላፊው፣ በተለይም ግጭቶች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ በሰላም ግንባታ ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል ። ድርቅና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ከመከሰታቸው አስቀድሞ ከወዲሁ የተቀናጀ የተፋሰ ልማት ሥራ መስራት መፍትሔ እንደሚያስገኝም ተናግረዋል ። በክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አማካኝነት ከስምንት ዞኖች የተውጣጡ አርሶአደሮች በተቀናጀ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ሥራ የልምድ ልውውጥ መደረጉንና ሥልጠና መሰጠቱን አመልክተዋል እንደ ኃላፊው ገለጻ ማህበሩ በዞኖቹ ለተከናወኑ ተግባራት 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ አድርጓል ። የደቡብ ክልል የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ሠራተኞች ተወካይና የሴክተር መስሪያ ቤቶች በጎ ፈቃደኛ ሠራተኞች አስተባባሪ አቶ ወልደአማኑኤል ጉድሶ የ49 ሴክተር መስሪያ ቤቶች በጎ ፈቃደኞች መድረክ መቋቋሙን ተናግረዋል ። "በእያንዳንዱ ሴክተር መስሪያ ቤት የሚገኙ አመራርና ሠራተኞች ቀይ መስቀል ማህበር እያከናወነ ያለውን ተግባር ተስማምተዋል" ያሉት ኃላፊው ሰብዓዊ ተግባር የማህበሩና የመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ዜጋ በመሆኑ በጎ ፈቃደኞቹ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል። የክልሉን እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ በመወከል የተገኙት ወይዘሮ አልማዝ ሐሰን በበኩላቸው ባለፈው በጀት ዓመት ተከስተው በነበሩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች ከደሞዛቸው በመቁረጥ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ። ሠራተኞቹ ድጋፋቸውን ለማጠናከር ከመግባባት ላይ መድረሳቸውንም ገልጸዋል። በመድረኩ የብሄራዊ ማህበሩና የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አካላት፣ ከክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ አስተባባሪዎችና ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን፣ የማህበሩን ሥራ ላገዙ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።