በቁልቢ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ ድንገተኛ ሞት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ፖሊስ መያዙን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በቁልቢ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ ድንገተኛ ሞት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ፖሊስ መያዙን አስታወቀ
ሐረር ኢዜአ ነሐሴ 16 / 2011- የቁልቢ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ መልዓከኃይል ቆሞስ አባ እንቁስላሴ ድንገተኛ ህልፈተ ሕይወት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 11 ሰዎችን በመያዝ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ድቪዝን ኃላፊ ኮማንደር ስዩም ደገፋ ለኢዜአ እንደገለጹት የገዳሙን አስተዳዳሪ የአሟሟት ሁኔታ ለማጣራት ከዞንና ከሜታ ወረዳ አቃቤ ህግና ፖሊስ የተውጣጣ ቡድን ተቋቁሞ ምርመራ በመደረግ ላይ ነው። በዚህም እስካሁን የተጠረጠሩ 11 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነም አመልክተዋል። መርማሪ ቡድኑም ወደዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል የተላከውን የአስክሬን ምርመራ ውጤት በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። የገዳሙ አስተዳዳሪ ህይወታቸው ባለፈ በበነገታው የአካባቢው ነዋሪዎች ከወረዳው አስተዳዳሪ፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ከዳረጉና የጋራ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ ከህግ አግባብነት ውጭ መንገድ መዝጋታቸውን ኮማንደር ስዩም አያይዘው ተናግረዋል። ከእዚህ በተጨማሪ ሌሎች የጸጥታ ችግሮችን በመፈጸም ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በተፈጠረው ግጭት አንድ የስምንት ዓመት ታዳጊ ሕጻን ሕይወቱ ማለፉንና በአራት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአሁኑ ወቅት በድሬዳዋ ህክምናቸውን እየተከታተሉ መሆኑንም ገልጸዋል። የገዳሙ አስተዳዳሪ መልዓከ ኃይል ቆሞስ አባ እንቁስላሴ ባለፈው ነሐሴ 12 ቀን 2011 ዓ.ም በገዳሙ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ድንገት ሕይወታቸው አልፎ መገኘቱ ይታወሳል። የቀብር ሥነስርአታቸውም ባለፈው ማክሰኞ በትውልድ ስፍራቸው መፈጸሙ ታውቋል ።