ቀጥታ፡

የኳታር መንግስት በአዲስ አበባ የሚገነባውን የኩላሊት ህክምና ሆስፒታል ሥራ በፍጥነት የመጀመር ፍላጎት አለው

ነሐሴ 16/2011 የኳታር መንግስት በአዲስ አበባ ለመገንባት ቃል የገባውን የኩላሊት ህክምና ሆስፒታል ግንባታ ሥራ በፍጥነት መጀመር እንደሚፈልግ አስታወቀ። የኳታር ልማት ፈንድ ለመጀመሪያው የሆስፒታሉ ግንባታ ሥራ 18 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድቧል። በኳታር የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ተበጀ በርሄ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ከኳታር ልማት ፈንድ የፕሮጀክት ኃላፊዎች ጋር ዛሬ ውይይት አድርገዋል። የጤና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ልዩ የፕሮጀክት አማካሪ ዶክተር ሰናይት በየነ እና የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የኩላሊት ሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር አዲሱ መልኬ በልዑካን ቡድኑ ውስጥ የተካተቱ ባለሙያዎች ናቸው። በውይይቱ የኳታር ልማት ፈንድ የልማት ፕሮጀክቶች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ሚስፈር ሃማድ አል ሻህዋኒ እና ሌሎች የተቋሙ ፕሮጀክት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። ከአሁን ቀደም በሁለቱ አገራት መሪዎች ስምምነት መሰረት የኳታር መንግስት በአዲስ አበባ የኩላሊት ሕክምና ሆስፒታል ለመገንባት የገባውን ቃል በአፋጣኝ ወደተግባር ለማሸጋገር በሁለቱ ወገኖች በኩል ዝርዝር ውይይት መደረጉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ግንባታውንም በፍጥነት ሥራ ለማስጀመር በውይይቱ ከመግባባት ላይ መደረሱም ተመልክቷል። በዚሁ ወቅት እንደተገለፀው የሆስፒታል ግንባታ ሂደቱ ሁለት ምዕራፎች የሚኖሩት ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ የህንፃ ግንባታውንና የባለሙያዎች ስልጠናን የሚያካትት ይሆናል። እነዚህን ሥራዎች ተፈጻሚ ለማድረግም የኳታር ልማት ፈንድ 18 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድቧል። የልዑክ ቡድኑ ከኳታር ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ከተለያዩ የጤና ተቋማት ኃላፊዎች ጋር በዘርፉ ትብብር ለማድረግ እንዲቻል የጎንዮሽ ውይይቶችን አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪም ልዑካን ቡድኑ በእድሳት ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት የጎበኘ ሲሆን፣ በኤምባሲ በሚገኘው የኮሚዩኒቲ መጠለያ ውስጥ ከሚገኙ ዜጎች ጋርም ውይይት ማድረጉን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም