ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ዙሪያ የሚመክር ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

ነሀሴ16/2011 በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ዙሪያ የሚመክር ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) በመካሄድ ላይ ይገኛል። በጉባዔው ከ200 በላይ የተለያዩ አገራት ምሁራን፣ የፖለቲካ ሊሂቃንና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው። ዛሬ ማለዳ በተጀመረው ጉባዔ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በንግግራቸው የኢትዮጵያ ሰላም መረጋገጥ ለአካባቢው የአፍሪካ ሀገራት ወሳኝ ነው ብለዋል። በመሆኑም ሰላምና መረጋጋት፣ የህግ የበላይነት እንዲሁም የህዝቦች ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል። የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦምቤኪም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት መሆኗን በመጥቀስ ዛሬም ሰላምና መረጋጋቷ ለሁሉም አገራት ወሳኝ ነው ብለዋል። በአገሪቷ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ቀጣይነት እንዲኖረውና የሰላም ተምሳሌት እንድትሆን በጋራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ቀጣይ እድሎችና ስጋቶች ላይ የሚመክረው ጉባዔ ዛሬና ነገ የሚካሄድ ሲሆን የተለያዩ አገራት ምሁራን ዓለም አቀፍ የለውጥ ተሞክሮዎችን ያቀርባሉ። በዛሬው እለትም የአሜሪካና ቱኒዚያ  ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፋቸውን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ምሁራንም የአገሪቷን ታሪካዊ የለውጥ አጋጣሚዎች አስመልክቶ ጥናታቸውን የሚያቀርቡ ይሆናል። በአገሪቷ አሁን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት አስመልክቶም በምሁራኑ መነሻ ፅሁፍ ቀርቦ እንደሚገመገም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም