ባለፉት የክረምቱ ወራት በደረሰ የጎርፍ አዳጋ 24 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ከመኖሪያው ተፈናቅሏል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት የክረምቱ ወራት በደረሰ የጎርፍ አዳጋ 24 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ከመኖሪያው ተፈናቅሏል
ነሀሴ16/2011 በክረምቱ ወራት በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች በደረሰ የጎርፍ አዳጋ 24 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ከቀዬው መፈናቀሉን የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። በቀሪው የክረምት ወቅትም በአንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በበኩሉ አሳስቧል። የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽንና ብሔራዎ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የጎርፍ አደጋ ስጋትን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ስጥተዋል። የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመና ዳሮታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ከክረምቱ ዝናብ ጋር ተያይዞ በወንዞችና በግድቦች ሙላት ሳቢያ ሞት፣ የንብረት መውደምና መፈናቀል ተከስቷል። ጉዳቱ በአፋር ክልል የከፋ መሆኑን የገለፁት አቶ ዳመነ በዚህ ክልል በተፈጠረው የጎርፍ አደጋ ከ15 ሺህ የሚልቁ ሰዎች ተፈናቅለዋል ብለዋል። አብዛኛዎቹ ተጎጂዎችም በክልሉ ፋንቲ ራሱ፣ ጋቢ ራሱ፣ አውሲ ራሱ ዞኖች የሚገኙት የቴሩ፣ ዱብቲ፣ ገልአሎና ዱሌቻ ወረዳ ነዋሪዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። በደቡብና አማራ ክልል አንዳንድ ወረዳዎችም ችግሩ ተከስቶ በርካታ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳሉት በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ ናዳና የመሬት መንሸራተት ተከስቷል። በጎርፉ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎች መንግስት የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመመገቢያና የመጠለያ ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። ኮሚሽኑ ክረምቱ ከመግባቱ አስቀድሞ የተደራጀ የጎርፍ መከላከል ግብረ ሃይል በማቋቋም አደጋው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል። ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ሃይለማርም በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ወራት በአገሪቱ የጣለው ዝናብ መጠኑ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል። ዝናቡ በተለይ ለክረምት ወቅት የግብርና ሥራ ከፍተኛ ጠቀሜታ የነበረው ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ግን በርካቶችን ለጉዳት የዳረገ ጎርፍ አስከትሏል ብለዋል። በቀሪው የክረምት ወቅትም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ህዝቡ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል። በተለይ በከተሞች አካባቢ ሊገጥም የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ የውሃ መውረጃ ቦዮችን በአግባቡ መጥረግ ያስፈልጋል ብለዋል።