ሌተናል ጀኔራል ቡርሃን የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ሸንጎ መሪ ሆነው ቃለ መሃላ ፈጸሙ

73
ኢዜአ ነሃሴ 15/2011ሀገሪቱን እስካሁን እየመራ ያለው ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሃላፊ ሌተናል ጀኔራል አብድል ፋታ ቡርሃን አዲስ የተመሰረተው ሉዓላዊ የሽግግር ሸንጎ መሪ ሆነው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል። ቡርሃን አምስት ወታደራዊ እና ሌሎች ስድስት የሲቪል ተወካዮች በድምሩ 11 አባላት ያሉትን ሉዓላዊ የሽግግር ሸንጎ ለሚቀጥሉት 21 ወራት ይመሩታል።
ለ39 ወራት በሚቆየው የሽግግር ጊዜ የሀገሪቱ መንግስታዊ ስራዎችን የሚያከናውኑ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትርና ካቢኔ እንደሚኖርም ይጠበቃል። ሱዳንን ለ30 ዓመት ያህል በፕሬዚዳንትነት የመሯት ኦማር አል በሺር ባሳለፍነው ሚያዚያ 2019 ከስልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ ነው አዲሱ የሽግግር መንግስት የተቋቋመው። የሱዳን የሽግግር ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሲቪል የሚሾም ሲሆን የመከላከያ እና የሀገር ውስጥ ሚኒስትሮች ከወታደሩ እንደሚሾሙ ተጠቁሟል። ሌተናል ቡርሃን የመጀመሪያዎቹን 21 የሽግግር ወራት የሽግግር ሸንጎውን የሚመሩ ሲሆን በሀገሪቱ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ያሉትን ቀጣይ 18 ወራት ደግሞ ሲቪሎቹ ይመራሉ። አሁን የሽግግር ሉዓላዊ ሸንጎው እና የካቢኔ አባል ሆነው የሚሾሙት በሀገሪቱ በሚካሄደው ምርጫ እንዳይወዳደሩ በወታደራዊና በተቃውሞ መሪዎች ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል። ምንጭ ፡-ቢቢሲ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም