የኢትዮጵያ የጤና ልዑካን ቡድን የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ዓመታዊ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው

66
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 15/2011 የኢትዮጵያ የጤና ልዑካን ቡድን በኮንጎ ብራዛቪል እየተካሄደ በሚገኘው 69ኛው የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ዓመታዊ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው። ጉባኤው ከትናንት በስቲያ የተጀመረ ሲሆን የ47 አገራት የጤና ሚኒስትሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። በጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን የተመራና ከፌዴራል እና ከክልል ጤና ቢሮ የተወጣጣ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። ዶክተር አሚር አማንና የልዑካን ቡድኑ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ለማጠናከር የጤና መረጃ አያያዝና አያያዝን ጠንካራና የተደራጀ ለማድረግ ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ልዑካን ቡድኑ መወያየቱ ተገልጿል። ክትባት፣ የመረጃ አብዮት እና የዘርፈ ብዙ የወረዳ ትራንስፎርሜሽን ስራዎች የትኩረት አቅጣጫዎች አድርጎ ለመስራትም ምክክር ተደርጓል። እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው ጉባኤ ላይ በአህጉሪቱ በጤና ዙርያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች፣ የተመዘገቡ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ የፓሊሲ አቅጣጫዎችና የጤና ስርዓትን ማጠናከር ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም