በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር ለበሽታና ለጎርፍ አደጋ ችግር ተጋልጠናል...በደሴ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር ለበሽታና ለጎርፍ አደጋ ችግር ተጋልጠናል...በደሴ ከተማ ነዋሪዎች
ደሴ ኢዜአ ነሀሴ 15 / 2011- በደሴ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ባለመኖሩ ለበሽታና ለጎርፍ አደጋ ችግር ተጋልጠናል ሲሉ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ተናገሩ። ከተማዋን ውብና ጽዱ ለማድረግ የህብረተሰቡ ያላሰለሰ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል። በደሴ ከተማ ሆጤ ክፍለ ከተማ የሚኖሩት አቶ እሸቱ ያሲን ለኢዜአ እንደገለጹት ህብረተሰቡ ያለአግባብ በየቦታው በሚጥለው ደረቅ ቆሻሻ ምክንያት በሚፈጠር መጥፎ ሽታ ለበሽታ እየተዳረጉ ነው። ደረቅ ቆሻሻና የፕላስቲክ ውጤቶችን በውሃ ማፋሰሻ ቱቦ ውስጥ ስለሚጣሉ በአሁኑ ወቅት ቦዮች ተደፍነው ለጎርፍ አደጋ መጋለጣቸውን ተናግረዋል። በተለይም ሆቴሎችና ተቋማት ተረፈ ምርቶቻቸውን በአግባቡ ከማስወገድ ይልቅ ጨለማን ተገን አድርገው ቆሻሻን በየሜዳው የሚጥሉበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል። የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶቹን በማደራጀት ጥበቃ እንዲያደረጉ ቢሞክርም ቆሻሻን መከላከል እንዳልተቻለና በእዚህም ጤናና ደህንነታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ተናግረዋል። የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ዳውድ ሀሰን በበኩላቸው ደሴ አንጋፋ ከተማ ብትሆንም የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቷ ኋላ ቀር መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ “በተለይ በመናኸሪያ ጀርባ፣ አራዳ፣ አሬራና አረብ ገንዳ አካባቢዎች ቆሻሻ በውሃ ማፋሰሻ ትቦዎችና በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ የሚጣል በመሆኑ ልጆቻችን እየታመሙ ነው” ብለዋል። በዚህ ምክንያት አንዲት ልጃቸው ታማ ለወጭ መዳረጋቸውን ነው የገለጹት። እንደ አቶ ዳውድ ገለጻ በአካባቢያቸው በደረቅ ቆሻሻ ምክንያት የውሃ መውረጃ ትቦዎች ተዘግተው በየመንገዱ ጎርፍ በመንገድ ላይ በመፍሰስ ለስጋት ዳርጓቸዋል። የደሴ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ሙሴ በበኩላቸው ከህብረተሰቡ የሚነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑን አምነዋል። ለመፍትሄው የህብረተሰቡ ትብብር አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት አቶ ብርሀኑ፣ ከተማ አስተዳደሩ በአምስቱም ከፍለ ከተሞች ደረቅ ቆሻሻ የሚያነሱ አስር ማህበራትን አደራጅቶ ወደስራ ማስገባቱን ገልጸዋል። “ማህበራቱ በየዕለቱ የከተማዋን ደረቅ ቆሻሻ በማንሳት የከተማዋን ጽዳትና ውበት ለመጠበቅ እየሰሩ ይገኛሉ” ብለዋል። በየጊዜው ከህብረተሰቡ በሚነሳው ቅሬታ መሰረት ችግሩ ጎልቶ በታየባቸው ቦታዎች በቀን ሦስት ጊዜ ቆሻሻ በማንሳት አካባቢውን ጽዱ ለማድረግ ቢሰራም ቆሻሻ መልሶ የሚጣልበት ሁኔታ መኖሩን አቶ ብርሃኑ አመልክተዋል። የተዘጉ የውሃ ማፋሰሻ ቦዮች በበጎ ፍቃድ ሥራ በተሰማሩ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲከፈቱ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። “ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት በዕድር፣ በዕምነት ተቋማትና በተለያዩ መድረኮች ጭምር ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት ህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱን እንዲያሻሻል እየተሰራ ነው” ብለዋል። የንግድ ቤቶችን የቆሻሻ አያያዝ፣ አወጋገድና አሰባሰብ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መመሪያ ተዘጋጅቶ እንዲደርሳቸው መደረጉንና መመሪያውን በተደጋጋሚ ጥሰው በተገኙ ግለሰቦች ላይ እስከ 10 ሺህ ብር መቀጣታቸውን አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት በቀን ከ40 መኪና በላይ ደረቅ ቆሻሻ የማንሳት አቅም መፈጠሩን ጠቁመው፣ ህብረተሰቡ የሚያመነጨውን ቆሻሻ ለእይታ ምቹ በሆነ ቦታ ላይ በአግባቡ በማስቀመጥ ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡ ጥቅም ላይ የዋለን የፕላስቲክ ጠርሙስ መልሶ የሚጠቀም ፋብሪካ በከተማው ሥራ መጀመሩን ገልጸው ይህም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል። ከተማ አስተዳደሩ በዓመቱ ለማንሳት ካቀደው 86 ሺህ ሜትር ኩብ ደረቅ ቆሻሻ እስካሁን ድረስ ከ70 ሺህ ሜትር ኩብ በላይ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ መቻሉ ተመልክቷል፡፡