ቀጥታ፡

በከተማዋ ባለቤት አልባ ውሾች ክትባት እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ገለጸ

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 14/2011 የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የእብድ ውሻ በሽታ መዛመትን ለመከላከል በአዲስ አበባ የሚገኙ ባለቤት አልባ ውሾች እንዲከተቡ እያደረገ መሆኑን ገለጸ። በከተማው የሚገኙ ባለቤት አልባ ውሾች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል። በኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ባዬ አሸናፊ እንደሚሉት፤ የጎዳና ተዳዳሪዎች የእብድ ውሻ ተጋላጭነት ከፍ ያለ በመሆኑ ይህንን ለመከላከል ያለመ ስራ እየተሰራ ነው። ባለቤት አልባ የሆኑ ውሾችን የመከተብ ስራ በኢንስቲትዩቱ በተጠናከረ መንገድ እንደሚካሄድ የገለጹት ዶክተር ባዬ ፤ የውሻ ባለቤቶች በበኩላቸው በእንክብካቤ የመያዝና የማስከተብ ተግባራቸውን ሳይዘናጉ እንዲያከናውኑ አስገንዝበዋል። በክረምት ወቅት ውሻዎች ምግብ ፍለጋ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበትና የመራቢያ ወቅታቸው በመሆኑ አንድ ላይ በሚሄዱበት ጊዜ በሽታው በስፋት ለመተላለፍ እድል እንደሚያገኝ አብራርተዋል። አንድ ውሻ ከአምስት እስከ አስር ሰው በአንዴ መንከስ መቻሉን የተናገሩት ዶክተር ባዬ፤ በዚህም ምክንያት ካላቸው የህክምና ክትባቶች ጋር ያለመመጣጠን ችግሮች አሉ ብለዋል። በመንግስት ወጪ ከሚገዛውና ኢኒስቲትዩቱ ከሚያመርታቸው የእብድ ውሻ በሸታ መከላከያ ክትባት መድሃኒቶች በተጨማሪ የተለያዩ አስመጪ ድርጅቶች ከውጭ እንደሚያስገቡ አስታውሰው፤ የውጪ ምንዛሬ እጥረት አስመጪዎች በሚፈለገው ልክ እያስገቡ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ችግሩ የሚፈጠረው ባለቤት አልባ በሆኑ ውሾች ብቻ ሳይሆን ባለቤት እያሏቸው በተገቢው መንገድ ክትትል በማይደረግላቸው ውሾች ጭምር እንደሆነ ዶክተር ባዬ ገልጸዋል። ''መፍትሄው ማስከተብ ብቻ ነው'' ያሉት ተመራማሪው፤ ውሻ ያላቸው ግለሰቦች ውሾቻቸውን የማስከተብ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ትምህርት ቤቶች ዝግ በመሆናቸው ልጆች በቤት አካባቢ መጫወታቸውን ተከትሎ ተጋላጭነታቸው እንደጨመረም ጠቁመዋል። የበሽታውን አሳሳቢነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር መደረግ ባሉባቸው ነገሮች ዙሪያ አስፈላጊውን መረጃ በግብርና፣ በማዘጋጃ ቤት፣ በፖሊስና በጤና ተቋማት በኩል እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩቱ በ2011 ዓ.ም ከ10 ሺህ በላይ ውሻዎች መከተብ ችሏል። የእብድ ውሻ በሽታ የየቫይረስ በሽታ ሆኖ ከፍተኛ የአንጎል መጉረብረብን በሰዎች እና በሌሎች ደመ-ሞቃት እንስሳት ላይ የሚያስከትል በሽታ ሲሆን ቅድሚያ ምልክቶቹ ትኩሳት እና በተነከሱበት ቦታ ማሳከክ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ሃይል የታከለባቸው የሰውነት እንቅስቃሴዎች፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ መሸበር፣ የውሀ ፍራቻ፣ የሰውነት ክፍልን ለማንቀሳቀስ አለመቻል፣ ግራ መጋባት፣ እና ህሊናን መሳት የበሽታው ምልክቶች ሲሆኑ እስከሞት የሚያደርስ ጉዳት ያስከትላል። የእብድ ውሻ በሽታ ወደ ሰዎች የሚተላለፈው በሌሎች እንስሳት ነው። በበሽታው የተበከለ እንስሳ ሌላ እንስሳ ወይም ሰው ሲቧጭር ወይም ሲናከስ የእብድ ውሻ በሽታ ሊተላለፍ ይችላል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም