በአገሪቱ 12 ኤርፖርቶች ላይ የመሳሪያዎች ፍተሻ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ነሀሴ 13/2011  የአውሮፕላኖች በረራ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን በመላ አገሪቱ በሚገኙ 12 ኤርፖርቶች ላይ ፍላይት ካሊብሬሽን እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ። ከሐምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የበረራ አጋዥ መሳሪያዎች ፍተሻ በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ጅግጅጋ፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ አክሱም፣ ሰመራ፣ አዋሳ፣ ጅማናና አርባ ምንጭ ኤርፖርቶች ነው። በአገሪቱ የተቋቋሙ የበረራ አጋዥ መሣሪያዎች በተወሰኑ ወቅቶች እንዲመረመሩና እንዲስተካከሉ ማድረግ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ቅድሚያ ከሚሠጣቸው ጉዳዮች አንዱ ነው። ውጤታማ የበረራ ሂደቶችን ለማረጋገጥ የሚያስችለው ይህ ፍተሻ የአውሮፕላን በረራን አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ እንደሚያደርግ የባለሥልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አንሙት ለማ ገልጸዋል። ባለሥልጣኑ ደህንነቱ የተጠበቀ በረራ እንዲኖር የወቅቱን ቴክኖሎጂ መሠረት ባደረጉ የመገናኛና የአየር ትራፊክ እንቅስቃሴ መሣሪያዎች አገልግሎት እየሠጠ መሆኑንም ተናግረዋል። የበረራ ቁጥጥር ምርመራ የሚካሄድባቸው በመሬት ላይ የተተከሉ የበረራ መርጃ መሣሪያዎች ማለትም የአውሮፕላን አቅጣጫና ያለበትን ርቀት የሚያሣውቁ፣ የማረፊያ ሜዳን ማዕከል የሚያሣዩና ሌሎችም መሣሪያዎች ናቸው።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም