በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ 8 ነጥብ 79 ኪሎ ግራም ወርቅ ተያዘ

129
ነሐሴ 13 / 2011 በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ 8 ነጥብ 79 ኪሎ ግራም ወርቅና የተለያዩ የውጭ አገር የገንዘብ ኖቶች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ። የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ እንደገለጹት በቁጥጥር ስር የዋለው 8 ነጥብ 79 ኪሎ ግራም ወርቅ፣ 41 ሺህ ዩሮ፣ 55 ሺህ ሪያል እንዲሁም ሁለት ተሽከርካሪዎች ይገኙበታል። በቁጥጥር ስር የዋለው በሶማሌ ክልል ሞምባስ ኬላ በኩል ከለሊቱ 10 ሰዓት ላይ በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ ሲል መሆኑን ገልጸዋል። የተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎችና የገንዘብ ኖቶች ዛሬውኑ ለብሄራዊ ባንክ ገቢ መደረጋቸውንም ተናግረዋል። ባለፈው ሀምሌ ወር ብቻ 134 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ኮንትሮባንድ የገቢና ወጪ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውሰዋል። የኮንትሮባንድ መከላከልና ህገ ወጥ ንግድ እንቅስቃሴ ቁጥጥር ንቅናቄ መጀመሩን ተከትሎ ክትትሉ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል። በ2011 ዓ.ም በየተሰራው የፀረ ኮንትሮባንድ ስራ ውጤት ማስመዝገቡን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ በ2012 ዓ.ም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ የፀጥታ አካላት፣ የጉምሩክ ሰራተኞችና ኀብረተሰቡ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል በጋራ እየሰሩ ነው። በ2011 ዓ.ም 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚገመት ወጪና ገቢ ኮንትሮባንድ እቃ መያዙን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም