ሴት የፓርቲ አመራሮችና አባላት ዴሞክራሲን ለማጠናከር በሚካሄደው እንቅስቃሴ ድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
ሴት የፓርቲ አመራሮችና አባላት ዴሞክራሲን ለማጠናከር በሚካሄደው እንቅስቃሴ ድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቁ
አዳማ ነሐሴ 13/ 2011 ሴት የፓርቲ አመራሮችና አባላት ዴሞክራሲን ለማጠናከር እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ድርሻቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳሰበ። የአመራሮችና የአባላትን አቅም የሚያጠናክር የአመራርና ተቋማዊ ለውጥ ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። የቦርዱ አባል ወይዘሪት ብዙወርቅ ከተተ በዚሁ ወቅት እንዳስገነዘቡት በአገሪቱ ዴሞክራሲን ለማስፋት እየተደረገ ባለው ሂደት ሴት የፓርቲ አመራሮችና አባላት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ 103 ፓርቲዎች ውስጥ በሴት የሚመራ አንድ ፓርቲ ብቻ መሆኑን አመልክተው፣ይህም የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ማሳያ ነው ብለዋል። ቦርዱ አመራሮችን ለማብቃት ከፓርቲዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በምርጫ ሕግ፣ በሥርዓተ ፆታ፣ በክህሎትና አቅም ግንባታ ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም የሴቶችን ፖለቲካዊ አቅም ለማሳደግ የስልጠና ፕሮግራሞችን ቀርፆ ወደ ሥራ መግባቱን ወይዘሪት ብዙወርቅ ገልጸዋል። በዚህም ረቂቅ የሕግ ማዕቀፎችና የማካተቻ አሰራሮች እየተዘረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ለአምስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ላይ ከሁሉም ፓርቲዎች የተውጣጡ የሴት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ተሳትፈዋል።