የአፄ ምኒሊክ 175ኛ የልደት በዓል በትውልድ ቀያቸው”እንቁላል ኮሶ” ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
የአፄ ምኒሊክ 175ኛ የልደት በዓል በትውልድ ቀያቸው”እንቁላል ኮሶ” ተከበረ
ደብረብርሃን ኢዜአ ነሐሴ 12/2011 የዳግማዊ አፄ ምኒሊክ 175ኛው የልደት በዓል ዛሬ በትውልድ ቀያቸው በባሶና ወራና ወረዳ በአጎለላ ቀበሌ ”እንቁላል ኮሶ” ተከበረ። የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድምአገኝ በበዓሉ ስነስርዓት ወቅት እንደገለጹት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ አሁን ኢትዮጵያ ለደረሰችበት ስልጣኔ በስልክ በዘመናዊ አስተዳደር፣ በትምህርት፣ በጤና እና በሀገረ ሰሪነት ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን አደራ ለመጠበቅ በተነሳሽነት የጀመረውን የሚኒሊክን የልደት በዓል እና የአድዋን በዓል ሲያከብር ሊኮራ ይገባል። አሁን ወጣቶች ከተሳሳተ ትርክት ወጥተው አንድነታቸውን በማጠናከር ለሀገር ሰላም፣ ልማትና እድገት ላይ በማተኮር ዘላቂ እድገት እንዲመጣ በተሰማሩበት የስራ መስክ እንዲተጉ አሳስበዋል። በቀጣይ ”የኢትዮጵያ ታሪክ በሰሜን ሸዋ ታላቅ የባህልና የታሪክ ሲፖዚየም ” በሚል እንደሚዘጋጅም ዋና አስተዳደሪው አስታውቀዋል። በበዓሉ ስነስርዓት የተገኙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዶክተር ዳኛቸዉ አሰፋ በበኩላቸው “ ቀደም ባሉት ዓመታት በዓሉን ለማክበር ስንጀምር የነበረው ስጋት አሁን ላይ ተገፎአል “ብለዋል የኢትዮጵ ቀደመት የስልጣኔ በር ከፋች ለሆኑት ለአፄ ምኒሊክ ውለታ ለመዋል አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሚያደርገው እንቅስቃሴ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ለመገንባት በጀት እንደተመደበ ያረጋገጡ መሆናቸውን ያመለከቱት ዶክተር ዳኛቸው ወጣቱ ሰላም ወዳድ በመሆን የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶለሳ በበኩላቸው አፄ ሚኒሊክ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ማስፋፋታቸውን ጠቅሰው ሀገርን መገንባት በአንድነት እንጂ በመከፋፈል ያለመሆኑን ታሪክን አተጣቅሰው የመላው የአፍሪካ ህዝብ ኩራት መሆናቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም የአጼ ምኒሊክ የትውልድ ስፍራ ለዓለም ህዝብ በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን አባት አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተክለስላሴ ከበደ “አባቶቻችን ጠላትን ለመከላከል ካደረጉት ተጋድሎ ባሻገር ለሀገሪቱ ስልጣኔ እድገት የጣሉት መልካም አሻራ ተዘንግቶ የጥላቻ ዘር እንዲበቅልበት ሲደረግ መቆየቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። በቀጣይ የአፄ ሚኒሊክም ሆነ የሸዋ ነገስታትን ታሪክ ለማስተዋወቅ ለሚደረገው ጥረት ባላቸው እውቀት ሁሉ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል። በበአፄ ሚኒሊክ የልደት በዓል ስነስርዓት ወቅተ ፈረሰኛ አርሶ አደሮች ፣ ከአዲስ አበባ፣ ከደሴ እና ከሌሎች የሀገሪቱ አከባቢዎች የተወጣጡ የታሪክ ተመራማሪዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።