ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማጠናከር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው

ነሐሴ 12/2011 በኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን በማጠናከር ዘርፉ ለአገሪቷ ምጣኔ ኃብታዊና ባህላዊ ልማት የበኩሉን ሚና የሚጫወትበትን መንገድ ለማመቻቸት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። የአገር ውስጥ ቱሪዝም ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ማስገኛ ስልት መሆኑን የሌሎች አገራት ልምድ ያሳያል። በተለይም ቻይና በዚህ ረገድ ተጠቃሽ አገር ስትሆን አርሶ አደሮቿን ጨምሮ አያሌዎች በየዓመቱ አገራቸውን የመጎብኘት ከፍተኛ ልምድ አዳብረዋል። ለአብነትም ባለፈው የአውሮፓ ዓመት ብቻ 764 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከአገር ውስጥ ቱሪዝም ማግኘት መቻሏን የአገሪቷ ዜና አውታር የዥንዋ ዘገባ ያመለክታል። ኢትዮጵያም ባለፈው ሳምንት የተከበረውን አረፋና  የመስቀል በዓላትን ጨምሮ በአገሪቷ የሚከበሩትን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔዎች እንደዚሁም ታሪካዊ ቅርሶች የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት የሚያስችሏትና እንደ ቻይና ሁሉ ገቢዋን ለማሳደግ የሚያግዙ ዓይነተኛ ስልቶች ናቸው። ሆኖም እነዚህ መስህቦች በበቂ መጠን ጥቅም ላይ እየዋሉ እንዳልሆነ ነው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ካሳሁን አያሌው በተለይ ለኢዜአ የገለፁት። ዘርፉ አገራዊውን የምጣኔ ኃብትና ማህበራዊ ልማት ለማገዝ የሚያስችል የተለያየ አቅም እንዳለው የሚናገሩት ባለሙያው የኃብት ክፍፍልን ማረጋገጥ፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከርና የዜጎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ማሳደግም በዘርፉ ሊሳኩ ከሚችሉት ተግባራት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አውስተዋል። ይህንን ሁኔታ መለወጥ እንዲቻል ታዲያ ሚኒስቴሩ በቅርቡ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ልማትን የሚከታተል ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት አዋቅሯል፤ አስፈላጊውን የሰው ኃይል በመመደብም ወደ ሥራ መግባቱን አቶ ካሳሁን አክለዋል። ከዚህም በተጨማሪ የ17 አገራትን የአገር ውስጥ ቱሪዝም ልማትና ትግበራትና ተመክሮ መሰረት ያደረገ አንድ ብሄራዊ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ልማት ሰነድ መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል። የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ስልቶችን የሚቀይሰው ሰነዱ በባለሙያዎችና በሚመለከታቸው አካላት አስተያየት ከዳበረ በኋላ በቅርቡ ሥራ ላይ እንደሚውልም አመልክተዋል። ባለፈው ሳምንት የተከበረውን አረፋን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚከበሩት የተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔዎች እንደዚሁም ታሪካዊ ቅርሶች የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት የሚያግዙ ኃብቶች ናቸው የሚሉት አቶ ካሳሁን፤ እነዚህን መስህቦች በመጠቀም በተደራጀ መልኩ ዘርፉን ለማሳደግ የሚሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያውያን የእስልምና ተከታዮች ዘንድ ከተከበረው የኢድ አል አድሃ ዓረፋ እና በመጪው መስከረም አጋማሽ ላይ የሚከበረውን የመስቀል በዓላት በጉራጌና ስልጤ ብሄረሰቦች ዘንድ ያላቸውን  ባህላዊ እሴቶች ለዓለም ለማስተዋወቅና በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች አድርጎ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ መጀመሩን የጉራጌ ዞን አስታውቋል። የጉራጌ ዞን ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አደም ሽኩር እንደተናገሩት በቅርስነት የማስመዝገቡ ተግባር እየተከናወነ ያለው ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ነው። የአረፋና መስቀል በዓላት በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ያላቸው ባህላዊ እሴቶች በዓለም ቅርስነት ቢመዘገብ የአገሪቷን ቱሪዝም ከማሳደግ ባለፈ መልካም እሴቶቹን በአገሪቷ ለማስፋፋትም ያግዛል ብለዋል። የዓረፋ በዓል መተሳሰብ፣ መረዳዳትና አንድነት የሚስተዋልበት፤ በጉራጌና ስልጤ ማህበረሰብ ዘንድም ትልቅ ክብር የሚቸረው ዓመታዊ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም