በአብሮነት ላይ የተመሰረተ የጋራ ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማውረስ እንሰራለን -- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በአብሮነት ላይ የተመሰረተ የጋራ ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማውረስ እንሰራለን -- ምሁራን
ሆሳዕና ኢዜአ ነሐሴ 12/2011 በአፍራሽ አጀንዳዎች ላይ ከማተኮር በአብሮነትና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ የጋራ ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማውረስ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ በወራቤ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ፡፡ በወቅታዊ ጉዳይ የኢዜአ ሪፖርተር የነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ምሁራን እንዳሉት ከዘረኝነት እና ከጥላቻ በመጽዳት የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ትውልድ ላይ በትኩረት መስራት ይገባል። በዩኒቨርስቲዉ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ መሀመድ አማን በሰጡት አስተያየት "ሰላም የሰፈነባት ጠንካራና የበለጸገች ሀገር እንድትኖረን ዕውቀትና ክህሎት ያለው ትውልድ ለመፍጠር እንሰራለን" ብለዋል። ይህ እንዲሆን መነጣጠል ሳይሆን አብሮነት፣ መተሳሰብንና ፍቅርን ማጎልበት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል። ለሀገር በማይጠቅሙ ጥቃቅን አጀንዳዎች ላይ ማተኮርን በመተው የጋራ ተጠቃሚነት ላይ በመሳታፍ ሀገሪቱን ከድህነትን ለማውጣት ትግሉ በሰላማዊ መንገድ ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “አባቶቻችን በመሰዋዕትነት ያቆዩልንን ሀገር ልማቷን በማስቀጠል ለትውልዱ ማስተላለፍ የኛ ኃላፊነት ነው” ብለዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በሰላም የአብሮነት የጋራ እሴቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደ ሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡ “በወቅቱ ተነጋግረን መተራረም ስንችል ጥቃቅንና ለማንም በማይጠቅም ጉዳይ ላይ ተጠምደን ሀገራችን የምትታወቅበትን በጎ ስም እያጠለሸን ነው” ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የቋንቋና ስነ ጽሁፍ መምህር ቶፊቅ ጀማል ናቸው፡፡ ለሀገራቸው ከፍተኛ ፍቅር የነበራቸው አባቶቻችን ጠንካራና ለሌሎች ምሳሌ የምትሆን ሀገር ቢያወርሱንም የነሱን ስራ በማስቀጠል በጋራ መኖር እንዳቀተ ተናግረዋል። "ከዘረኝነት እና ከጥላቻ ጸድተን የበለጸገች ሀገር ለልጆቻችን በማውረስ የነሱን አደራ ለማስከበር በትኩረት መስራት ይገባናል" ብለዋል። በዩንቨርስቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ሙከሚል አብራር በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር በስነ ምግባር የታነጸ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የተሰጣቸው ኃለፊነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "መልካም ፍሬ በማፍራት የተሻለ ስራ መሰራት ይኖርበታል " ያሉት ዲኑ ከጎሰኝነት ይልቅ አብሮነትን ሊያጠናክር የሚችል ተግባራት ላይ ትኩረት አድርገው በመስራት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡