ቤዛ ተስፋዬ የኢትዮጵያ ጠፈር ሳይንስ ማህበረሰብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ

115
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010 ወይዘሮ ቤዛ ተስፋዬ የኢትዮጵያ ጠፈር ሳይንስ ማህበረሰብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው መሾማቸውን ስፔስ አፍሪካ የተባለ ድረ-ገጽ ዘገበ። የቀድሞ የአፍሪካ የጠፈር ሳይንስ ጀነሬሽን ምክር ቤት ክልላዊ አስተባባሪና በአፍሪካ በጠፈር ሳይንስ ኢንዱስትሪ ከሚገኙ 13 ሴቶች መካከል አንዷ የሆኑት ቤዛ ተስፋዬ የኢትዮጵያ ጠፈር ሳይንስ ማህበረሰብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ተሹመዋል። ወይዘሮ ቤዛ አለም አቀፍ ጥናትና አለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከሂልኮ የኮምፒውተር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት በኮምፒውተር ሳይንስ ከፍተኛ ዲፕሎማና የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ዝግጅት አላቸው። በኢትዮጵያ የጠፈር ሳይንስ ማህበረሰብ ከተመሰረተበት እ አ አ ከ2004 ጀምሮ ከሌሎች 46 መስራች አባላት ጋር በመሆን የጠፈር ሳይንስ ትምህርትና ግንዛቤን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማጎልበት በተደረገው እንቅስቃሴ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በዘርፉ ባላቸው አበርክቶ ከተለያዩ አለም ዓቀፍ ማህበራት ሽልማት እንደተበረከተላቸው ለማወቅ ተችሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም