የሽሬ ካምፓስ የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶችን በእርዳታ አገኘ

77
ነሐሴ 11/2011 በአክሱም ዩኒቨርስቲ የሽሬ ካምፓስ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶችን በእርዳታ አገኘ። ካምፓሱ ድጋፉን ያገኘው ከካናዳ መንግስት የማአድን ዘርፍ ትምህርትና ስጠልና ማጠናከርያ ፕሮጀክት  መሆኑን የካምፓሱ ዲን አቶ መአርግ በላይ ገልጸዋል። የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶቹ በተለይ በካምፓሱ ስር ለሚገኘው የስነ ምድርና ማአድናት ምህንድስና የትምህርት ክፍል አገልግሎት የሚውሉ ናቸው ብለዋል። በእርዳታ ከተለገሱት የትምህርት ቁሳቁሶች መካከል18 ዘመናዊ ጂፒኤሶችን ጨምሮ 45 ኮምፒዩተሮችን ፣ኮምፓሶችንና ሌሎች ለማአድን ዘርፍ አገልግሎት የሚሰጡ መሳሪያዎች ይገኙበታል ። ቁሳቁሶቹ በጂኦሎጂ፣ በማአድንና በሚኒራል ፕሮሰሲንግ ለሚያስተምራቸው ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለመስጠት ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ዲኑ ተናግረዋል። በርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የአክሱም ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፀሓየ አስመለሽ እንዳሉት ከካናዳ መንግስት የተገኙ የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች በቀጣይ ሦስት አመታት ውጤታማ የተግባር ትምህርት ለመስጠት የሚያግዙ ናቸው። በኢትዮጵያ የፕሮጀክቱ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ሙኒሽ ፐርሱድ  እንደገለፁት ፕሮጀክቱ ለአክሱም፣ለመቀሌና ለአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች ለማአድን ዘርፍ የሚያገለግሉ የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ እያደረገ ነው ። የዚሁ አካል የሆነው ድጋፍም በአክሱም ዪኒቨርስቲ ስር ላለው የሽሬ ካምፓስ ዛሬ የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ በባህላዊ መንገድ በደለል ወርቅ ምርት መሰብሰብ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የእለት ተእለት ፍለጋቸውን የሚያቃልልላቸው አነስተኛ የወርቅ ማምረቻ መሳርያዎች በማቅረብ በዘርፉ ውጤታማ እንዲሆኑ የቴክኒክና የምክር አገልግሎት ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ዋና ዳይርክተሩ ተናግረዋል ። በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲ የእርዳታ ክፍል ሃላፊ ሚስቴር ኢቫን ሮበርትስና የማአድንና ነዳጅ ሚኒስተር የምርምርና ልማት ዋና ዳይሪክተር ዶክተር ግርማ ወልደትንሳኤ የተመራ ቡድን በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በአስገደ ፅምብላ ወረዳ ልዩ ስሙ “ህፃፅ” በተባለ ቦታ በባህላዊ መንገድ የሚሰበሰበውን የደለል ወርቅ ጎብኝቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም