ቀጥታ፡

ኡጋንዳ የአባይ ወንዝን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የያዘችውን አቋም ኢትዮጵያ አደነቀች

ነሀሴ 11/2011 ኡጋንዳ የአባይ ወንዝን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የያዘችውን አቋምና የምትጫወተውን ቁልፍ ሚና ኢትዮጵያ እንደምታደንቅ በኡጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለምጸሃይ መሰረት ገለጹ። አምባሳደሯ ይህን የተናገሩት ሶስተኛው የኢትዮ-ኡጋንዳ የጋራ የሚኒስትሮች ጉባኤ ከተካሄደ በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው ባደረጉት የእራት ግብዥ ላይ ነው። የናይል ቤዚን ኢኒሸቲቭን መቀመጫ የሆነችው ኡጋንዳ የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንድትቀጥል አምባሳደሯ መጥቀሳቸውን ኒው ቪዥን ኡጋንዳ በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል። አገሮቹ ብሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ ሙሉ አባል ሲሆኑ ኤርታራ በታዛቢነት ተካታበታለች። “ፕሬዝዳንት ዩሪ ሙሴቪኒ የተፋሰሱ አገሮች ከናይል ወንዝ ፍትሃዊ አጠቃቀምን፣ በናይል ወንዝ የመጠቀም መብትን በተመለከተ በያዙት አቋም ደስተኛ ነን" ብለዋል። ኡጋንዳ የትብብር ማዕቀፉ ተግባራዊ እንዲሆን የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንድትገፋበት ድጋፋችንን እንሰጣለን” በማለት አምባሳደር አለምፀሃይ ተናግረዋል። ስምምነቱ የናይል ቤዚን ተፋሰስ አገራት በወንዙ ላይ እኩል የመጠቀም መብት እንዲኖራቸውና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በጋራ እንዲንከባከቡ የሚያስችል መሆኑንም አምባሳደሯ ጠቅሰዋል። የሁለቱ አገሮች ሚኒስትሮች ከፕሬዝዳንት ዩሪ ሞሴቪኒ ጋር በመገናኘት ለሃሳባቸው መቋጫ አስቀምጠዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም