ቀጥታ፡

በሀገራዊ ለውጡ ላይ ግንዛቤን በማሳደግ የኢንዱስትሪን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው

አዳማ (ኢዜአ) ነሀሴ 10 ቀን 2011 በሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ግንዛቤን በማሳደግ የኢንዱስትሪን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ2011 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምና የ2012 ዓ.ም መነሻ ዕቅድን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቢሾፍቱ ከተማ እየገመገመ ነው። የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቱ በእዚህ ወቅት እንዳሉት የተቋሙ የሰው ኃይል አገሪቷ የያዘችውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተረድቶ ውጤታማ ስራ እንዲሰራ ግንዛቤውን ማሳደግ ይገባል። በተለይ በእቅድና ስትራቴጂ ላይ ግንዛቤውን በማሳደግ ለተፈጻሚነቱ መረባረብ እንዳለበት ነው የተናገሩት። "የኢንዱስትሪ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ የሚቻለው አገሪቷ እየሄደችበት ያለውን የለውጥ ጉዞ በትክክል መገንዘብ ሲቻል ነው" ብለዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአደረጃጀት፣ በአሰራርና በሥራ አፈጻጸም ላይ ያሉትን ችግሮች በመቅረፍ በሀገሪቱ ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት እና የስራ ስምሪት እንዲረጋገጥ በማድረግ በኩል አበረታች አፈጻጸም መታየቱንም ተናግረዋል። በአሰሪና ሠራተኛ መካከል  የተሻለ ግንኙነት እንዲኖርና ለኢንዱስትሪዎች ውጤታማነት በጋራ እንዲረባረቡ ከማድረግ አንጻር በህግ፣ በአሰራርና በአደረጃጀቶች ላይ ወሳኝ ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል። እንደ ወይዘሮ አየለች ገለፃ ዓመቱ በኢንዱስትሪዎችና ኢንተርፕራይዞች መካከል ጥሩ ግንኙነት የተፈጠረበት ነው። በአሰሪና ሠራተኛ መካከል ጥቅምና መብትን ከማስጠበቅ አንጻር ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ማፅደቅ በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑት ተግባራት መካከል እንደሚጠቀስም ገልጸዋል። እንደሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ አዋጁን ተፈጻሚ ለማድረግ ህጎችና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ስራውን በበላይነት የሚመራ ቦርድ የማደራጀት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል። ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ከሃገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከባለድርሻ አካላት በጋራ በመሆን ጥናት እያካሄደ ነው። የውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923 / 2008ን ወደ ስራ ለማስገባትና ከተቀባይ አገራት ጋር የነበረው ድርድርና ስምምነት ውጤታማ ለማድረግ በባጀት ዓመቱ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራባቸው ዋነኛው መሆኑንም ጠቁመዋል። በዚህም ከሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ ጆርዳንና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ የሰው ኃይሉ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ወይዘሮ አየለች ተናግረዋል። በመድረኩ ላይ ጽሁፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ በበኩላቸው "የሰራተኞችን አመለካከትና አስተሳሰብ በመቅረጽ ውጤታማ ስራ መስራት ይገባል" ብለዋል። መሪዎች መልካም አስተዳደርን በተቋማቱ በመዘርጋት አመለካከት የመቀየር እንዲሁም የሰራተኛውን እውቀትና ጉልበት አቀናጅቶ ስራ ላይ ማዋል ከመሪዎች የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል። "እውቀትና ተግባር በስራ ላይ ካልዋለ ሃብት አይደለም" ያሉት ፕሮፌሰር መንገሻ አገሪቷ ያላትን ትልቁ የሰው ሃብት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል ። በቢሾፍቱ ከተማ ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው መድረክ ላይ ከ400 በላይ የሚሆኑ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም