ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሰላም ግንባታና የብሄራዊ መግባባት ሂደት ሴቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 10/2011 ሴቶች በኢትዮጵያ በሚከናወነው የሰላም ግንባታና የብሄራዊ መግባባት እንቅስቃሴ የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ። የኢትዮጵያ የሴቶች ፌዴሬሽንና የሰላም ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት አገር አቀፍ የሰላም ጉባኤ በመካሄድ ላይ ነው። በጉባኤው መክፈቻ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን እንደተናገሩት፤ አገራዊ የሰላም ግንባታና ብሄራዊ መግባባት መፍጠር በአንድ ተቋም ብቻ የሚከናወን ሳይሆን ሁሉንም ህብረተሰብ ያማከለ ነው። ''በኢትዮጵያ የአብሮነት፣ የመቻቻልና የመከባበር እሴቶችን በማጣት የአገሪቱ አንድነት አደጋ ላይ ሆኖ ለምን ዝም አልን? ከመካከላችን የግጭት ነጋዴዎችን አውጥተን ህዝቡ እንዳይጎዳ ለማድረግ ለምን አቃተን?'' ሲሉ በጉባዔው የተገኙ ሴቶችን ጠይቀዋል። በአለም አቀፍ ደረጃ የሰላምና መረጋጋት እጦት በተለያዩ አገሮች በተፈጠረበት ወቅት ሴቶች አገራቸውን ወደ ሰላምና መረጋጋት በመመለስ ረገድ ጉልህ ሚና መጫወታቸውንም አንስተዋል። ሴቶች የአገርን ሰላም ለማስጠበቅ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ተገንዝበው ለሰላም ግንባታ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ በበኩላቸው "ሴቶች የሰላም አምባሳደሮች እንደመሆናችሁ መጠን ቤታችሁ በግጭት ለተጠቁ  ስንት ሰዎች መጠጊያ ኤምባሲ ሆነ?" ሲሉ ጠይቀዋል። “በጎረቤታችሁና በምትኖሩበት አካባቢ ሰዎች ጥቃት ሲደርስባቸው ዝም አትበሉ፤ ድምጻችሁን አሰሙ፤ ድምጻችሁ የአደባባይና የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ማድመቂያ ብቻ አይሁን” በማለት አሳስበዋል። “ሴት የላከው ሞት አይፈራም" የሚለውን አባባል "ሴት የላከው ሞት አይሰራም" ወደ ሚል አባባል ለመቀየር መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። “እኛን በማባላት እንጀራ ለሚበሉ ሰዎች ጆሯችሁንና ቤታችሁን ከፍታችሁ አታስገቡ” ብለዋል። የጉባኤው ተሳታፊዎችም በየአካባቢው ያሉትን ችግሮች በመረዳትና ለሰላም መደፍረስ ምክንያት የሚሆኑ ችግሮችን በመለየት ሰላም ለማስፈን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል። የህዝቦች መፈናቀል፣ ግጭትና የሰላም እጦት ከነበረባቸው አካባቢዎች የመጡ ሴቶችም የሰላም እጦትን አስከፊነትን ገልጸው የሰላም ዋጋና አስፈላጊነት ምን ያህል አንገብጋቢ መሆኑን በችግሩ ወቅት መገንዘባቸውን አንስተዋል። ለህዝቦች አንድነት የሚያግዙ ማህበራዊ እሴቶች እንዲያንሰራሩ በማድረጉ ረገድም ሴቶች ግንባር ቀደም በመሆን እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አንድነት ለድርድር የማይቀርብ ጥያቄ መሆኑን በመረዳት ማህበራዊ ሚዲያዎች ሰላም ለመፍጠር እንጠቀምባቸው የሚሉ ሀሳቦችም ከተሳታፊዎቹ ተነስቷል። ሴቶች በየአካባቢያቸው ጠንካራ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ስለ ሰላም ማስተማርና ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ተገልጿል። በዚህ ዓመት ከህዳር አጋማሽ ጀምሮ ለአንድ ወር ከዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 22 የሰላም አምባሳደር እናቶች ቡድን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመዘዋወር ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተግባር ማከናወናቸው ይታወሳል። ”አባቶቻችን ፍቅርን እንጂ ጥላቻን ያላስተማሩን በመሆኑ ይህን መጥፎ የዘረኝነት አመለካከት በርብርብ ማጥፋት ይገባል” ማለታቸውም ይታወቃል። በጉዟቸውም ከክልል የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከህብረተሰቡ እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር በህዝቦች መካከል ሰላማዊ ግንኙነትና አንድነት እንዲኖር የሚያስችል ውይይት አካሂደው ውጤታማ ስራ ሰርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም