ቀጥታ፡

በትግራይ የተጠያቂነት ኮንፈረንስ ውጤት እያስገኘ ነው

መቐለ (ኢዜአ) ነሐሴ 10 ቀን 2011 በትግራይ ክልል በየዓመቱ ሲካሄድ የነበረው የተጠያቂነት ኮንፈረንስ የመንግስትና የህዝብ ሀብት ለታቀደለት ዓላማ በወቅቱ እንዲውል እያገዘ መሆኑ ተጠቆመ። የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ሦስተኛ ምዕራፍ መርሀ ግብር በትግራይ ክልል ደረጃ በይፋ ለማስጀመር የሚያስችል የማስተዋወቂያ መድረክ ትናንት በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል። የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ የምስራች ብርሃኑ በክልሉ በየዓመቱ የተካሄዱት የተጠያቂነት ኮንፈረንስ የመንግስት ሃብትና ንብረትን ለታለመለት ዓላማ በወቅቱ እንዲውል እገዛ እያደረገ መሆኑን  ገልጸዋል። የተጠያቂነት ኮንፈረንስ ከዚህ ቀደም በክልሉ በስፋት ይታይ የነበረውን የኦዲት ግኝትና የፕሮጀክቶች በጀት ብክነት እየቀነሰ እንዲመጣ ማስቻሉን ምክትል አፈ ጉባኤዋ አመልክተዋል። ከዚህ ቀደም የሒሳብ ምርመራ እንዳይደረግ ምክንያት በመፍጠር ያስቸግራሉ ሲባሉ የነበሩት መንግስታዊ ተቋማት በየዓመቱ በሚካሄደው የተጠያቂነት ኮንፈረንስ ላይ እንዲጠየቁ በማድረግ ችግሩን ሊወገድ ማስቻሉን ተናግረዋል። እንዲሁም ተቋማቱ በክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎችና በየደረጃው ያሉት አመራሮች ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርጉባቸው በማድረግ የህዝብና የመንግስት ሃብትን  ቆጣቢ በሆነ መልኩ ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉ ለማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም የክልሉ መንግስት ለጀመረው ጥረት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርም ወይዘሮ የምስራች ተናግረዋል። እንደ አርሳቸው ገለጻ ፕሮግራሙ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት የሚቀጥል ሲሆን፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመጠጥ ውሃ ፣ በገጠር መንገድና በግብርና ዘርፎች በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ላይ ከእቅድ እስከ ትግበራ ድረስ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ ነው። እንዲሁም በልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ተጠቃሚው ህብረተሰብና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም አመልክተዋል። በኢትዮጵያ የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም የአቅም ግንባታና የስልጠና ባለሙያ አቶ ወርቅነህ ደነቀው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራሙ በአምስቱ መሰረታዊ አገልግሎቶች ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 500 ወረዳዎች እየተተገበረ ነው። በእዚህም መንግስት የሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች የህዝቡን ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ ስለመሆናቸውና አፈፃፀማቸውን በተመለከተም በየጊዜው እንዲያውቁ አቅም የመገንባት ስራ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል። ፕሮግራሙን ለማስጀመር ትናንት በተዘጋጀው መድረክ ላይ በክልሉ የሚገኙ የሲቪክ ማህበራትና የማህበረሰብ ጥምረት አመራሮች፣ የመንግስት አስፈፃሚ አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄደው ይኸው ፕሮግራም በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር በኩል የሚተገበር መሆኑንም ታውቋል። በትግራይ የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ሄኖክ ክፍሌ እንደገለጹትም በክልሉ ፕሮግራሙ በ24 ወረዳዎች ውስጥ አንደሚከናወን ተናግረዋል። የማህበራዊ ተጠያቂነት በየደረጃው እንዲኖር እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያለው አሰራርን ለማጎልበት ለሚሰራው የግንዛቤ የማስጨበት ስራ ስድስት ሚሊዮን ብር መመደቡን ገልጸዋል። የምክክር መድረኩ ህዝብና መንግስት ተቀራርበው ለመስራት የጀመሩትን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑን የገለጹት ደግሞ በትግራይ የሲቪክ ማህበራት ጥምረት ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሚካኤል ገብረመድህን ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም