አመራሩ ፈታኝ ሁኔታዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ እንዲቀይር ተጠየቀ

65
ዲላ ኢዜአ ነሃሴ 10/2011 አመራሩ ፈታኝ ሁኔታዎችን ወደ መልካም አጋጣሚዎች በመቀየር የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሰራት እንዳለበት በጌዴኦ ዞን የአመራሮች ውይይት መድረክ ተሳታፊዎች ገለፁ የክልል አደረጃጀት ጥያቄን ለመመለስ በተጠናው ጥናት ላይ የጌዴኦ ዞን አመራሮች የውይይት መድረክ ዛሬ በዲላ ከተማ ተጀምሯል። በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ክልል ውሃ ፣ ማዕድንና ኢኔርጂ ቢሮ ሃላፊና የደኢህዴን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አንተነህ ፍቃዱ እንዳሉት ክልሉ ባለፉት ጊዜያት ካሳለፋቸው የትግል ምዕራፎች በተለየ መልኩ በመንታ መንገድ ላይ ይገኛል ብለዋል ። አመራሩ አሁን በክልሉ የሚስተዋሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን ወደ መልካም አጋጣሚዎች በመቀየር የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል። አመራሩ በተለይ ውስን ሙሁራን የሚያራምዱትን አጀንዳ በጥንቃቄ በመመርመር የክልሉን ህዝብ ዘላቂ ሰላም ሊያረጋግጡ የሚችሉ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገቡ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ጥልቅ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል ። በክልሉ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ በጎ ተጽዕኖ በማሳደር ህዝብ የጣለብንን ሃላፊነት በተግባር በመፈጸም በክልሉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መቀየር ይገባል ብለዋል። በተለይም በክልሉ እየተስፋፋ የመጣውን በክልል የመደራጀት ጥያቄ የምልአተ ህዝቡን ጥቅምና ሰላም በጠበቀ መልኩ እንዲመራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል። የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው የዞኑ ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም የህዝቡን ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ የሚችል ሃሳብ ማፍለቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የትኛውንም የመዋቅር ጥያቄ የህዝቦችን ሁለተናዊ ተጠቀሚነት የሚያረጋግጥና ሰላም የሚያሰፍን መሆን አለበት ብለዋል። ለሶስት ቀናት በሚቆየው መድረክ ከዞንና ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም