ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አገኘሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አገኘሁ አለ
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 10 /2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2011 በጀት አመት ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ። ባንኩ የ2011 በጀት አመት የእቅድ አፈጻጸሙን በአዲስ አበባ ከሰራተኞቹ ጋር እየገመገመ ነው። የባንኩ ፕሬዝዳንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ባጫ ጊና በዚሁ ወቅት እንዳሉት በበጀት አመቱ የዋና ዋና እቅዶች አፈጻጸም አበረታች ነበር። ከዚህ ውስጥ ባንኩ በበጀት አመቱ 17 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ትርፍ በማግኘት ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ካገኘው 10 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር የ7 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው። በተመሳሳይ የባንኩ ሃብት 145 ቢሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት ጠቅላላ ሃብቱ 712 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል። ይህም ባንኩ በእቅድ ይዞት ከነበረው 668 ቢሊዮን ብር የ44 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ነው የገለጹት። የተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ መጠንን በእቅድ ተይዞ ከነበረው ከ87 ቢሊዮን ብር በላይ ከ89 ቢሊዮን ብር በላይ ማሳደግ መቻሉንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው ከ86 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው። የባንኩ አጠቃላይ ክምችት ከ541 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱንም ነው ፕሬዝዳንቱ የጠቆሙት። የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ በኩልም በበበጀት አመቱ ከውጭ ንግድ፣ ከውጭ ሃዋላ እና ከብሔራዊ ባንክ ከተላለፈ አጠቃላይ 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ተናግረዋል። በእነዚህና በሌሎችም የእቅድ አፈጻጸሞች ባንኩ በበጀት አመቱ አበረታች ስራዎች መከወኑን ነው የተናገሩት። ባንኩ በዓመቱ 129 ቢሊዮን ብር ብድር የሰጠ ሲሆን የተበላሸ ብድር ከስድስት ቢሊዮን ወደ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ዝቅ ማለቱም ተነግሯል። ይሁንና በዓመቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኔትወርክና በተለያዩ የአሰራር ስርዓት መጨናነቆች ምክንያት ፈጣን አገልግሎት የመስጠት ችግሮች ሲያጋጥሙት፤ ደንበኞቹም ቅሬታቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ይታወሳል። ፕሬዝዳንቱ ባንኩ ከኔትወርክ ጋር በተገናኘ በየጊዜው ለሚከሰተው ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ምን እየሰራ ነው በሚል ከኢዜአ ለተነሳላቸው ጥያቄ የሲስተም ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው እስከ ስድስት ወር እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል። የተቀማጭ ገንዘብና የውጭ ምንዛሬን፣ እንዲሁም የደንበኞችን ብዛት ማሳደግ እና መሰል ተግባራት በቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ይሆናሉ ተብሏል። ባንኩ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በበጀት አመቱ 157 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት ጠቅላላ የቅርንጫፍ ብዛት 1 ሺህ 444 መድረሱ ተገልጿል። ባንኩ እያካሄደ ያለው የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ የሚቀጥል ሲሆን ስራዎችን በመገምገም አቅጣጫዎች ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።