የእግር ኳስ ሊግ ውድድሩን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ማስቀጠል ችግር ያስከትላል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የእግር ኳስ ሊግ ውድድሩን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ማስቀጠል ችግር ያስከትላል ተባለ
ነሀሴ 9/2011 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሊግ ውድድሩን አሁን ባለው የአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ማከናወን ብዙ የማያራምድና ችግሮች ያሉበት መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ። የአዲስ አበባ እግር ኳሰ ፌዴሬሽን ባደረገው ጥናት መሰረት የአገሪቷን እግር ኳስ ከችግር ለማውጣት አሁን ያለው የሊግ አደረጃጀት መቀየር እንዳለበት አመልክቷል። ፌዴሬሽኑ ባደረገው ጥናት በ44 የተለያዩ ሊግ የሚሳተፉ የፕሪሚየር ሊግ፣ የከፍትኛ ሊግና አንደኛ ሊግ ክለቦችና ሌሎች ባለደርሻ አካላት የመረጃ ግብአት ተሰብስቧል። የጥናቱ አቅራቢዎች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እንደገለጹት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚመራው የሊግ ውድድሩ አወቃቀር አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ መቀጠል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በጥናቱ እንዳመለከቱት ክለቦች በየክልሉ ተዘዋውረው ጨዋታቸውን ማካሄዳቸውና የአንዳንድ ክለቦች ስያሜ የብሔር ስያሜን መያዙ የክለቦች ህልውና ላይ አደጋ ውስጥ መጣሉን አቶ ገዛኸኝ ያብራራሉ። አደረጃጀቱ ክለቦች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው መጫዋታቸው ለከፍተኛ ወጪ መዳረግ፣ ለፀጥታ ችግርና ስጋት ዳርጓቸዋል። ክለቦች በሚገጥማቸው ከፍተኛ ወጪ ምክያት ሊጉ ከተቋቋመ ጀምሮ 18 የሚሆኑ ክለቦች መበተናቸውን ጥናቱ አመላክቷል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያስተዳድራቸው ክለቦች በዓመት በአማካይ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደረጋሉ። ከዚህም ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው ከመንግስት የሚበጀት ሲሆን ከወጪው አንጻር እግር ኳሱ በሚፈለገው መጠን እድገትና መሻሻል አለማሳየቱን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድንም ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር በሚያወጣው ደረጃ በ1999 እና 2000 ዓ.ም 100ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከ2000 ዓ.ም በኋላ ደግሞ 150ኛ ደረጃ ላይ በመድረስ አሽቆልቁሏል። በመሆኑም የሊጉ አደረጃጀት በየክልሉ የውስጥ ውድድር ተደረጎ የማጠቃላያ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ቢደረግ ሲል በጥናቱ ተመልክቷል። የሊጉ አደረጃጀት በፖለቲካ ተፅዕኖ ውስጥ በመውደቁ እግር ኳሱ መሻሻል አላሳየም ያሉት ደግሞ የቀድሞው የደደቢት አሰልጣኝ አስራት ሃይሌ ናቸው። በቀጣይ የክለቦች ስያሜ ከብሔር ስያሜ ወጥቶ በሌላ ስም በተካ ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የዓለም አቀፉን የእግር ኳስ ማህበር መርህ የተከተለ አደረጃጀትን መከተል እንዳለበትም ጠቁመዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታተም እንደቀድሞው የኢትዮፓ ሻምፒዮና ውድድር መርሃ ግብር ቢቀጥል የተሻለ መሆኑንም ገልፀዋል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እንዳሉትም እግር ኳሱን ለማሻሻል ፌዴሬሽኑ በባለሙያ መመራት ይኖርበታል። እግር ኳሱ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ተላቆ አደረጃጀቱም ተሻሽሎ መቀጠል አለበት ሲሉም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች አሁን ባለው የሊጉ አደረጀጃት ውድድር መቀጠል እንደማይፈልጉ ማሳወቃቸው ይታወቃል። ሁለቱ ክለቦች የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያስተደድራው ሊግ ውድድራቸውን ለማድርግ ማሰባቸውንም አሳውቀዋል። የአዲስ አበባ እግር ካስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ በለጠ ዘውዴ ክልሎች የውስጥ ውድድሮችን አካሂደው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ቢካሄድ በሚለው እስማማለሁ ብለዋል። የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ቢካሄድ ለእግር ኳሱ መሻሻልና እድገት አጋዥ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ መሳተፍ ካልፈለጉ ፌዴሬሽኑ ተቀብሎ የማወዳደር ሃላፊነት እንዳለበትም አምነዋል። ለዚህም ፌዴሬሽኑ ሙሉ ዝግጅት ማደረጉን አቶ በለጠ ተናግረዋል።