የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ነገ በኤርትራ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ነገ በኤርትራ ይጀመራል
ነሀሴ 9/2011 የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ከ15 ዓመት በታች የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ነገ ነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓም በኤርትራ አስመራ ከተማ ይጀመራል። ኤርትራ በአጠቃላይ አስር አገራት የተሳተፉበትን የዘንድሮው ሴካፋ ውድድር ስታዘጋጅ ይህ የመጀመሪያዋ ነው። የሴካፋ ከ15 በታች የወንዶች ውድድር ነገ በ8:00 ሰዓት ኬንያ ከሶማሊያ፤ አዘጋጇ አገር ኤርትራ ከብሩንዲ ጋር በአስመራ ከተማ በሚያካሄዱት ጨዋታ ነው የሚጀመረው። በውውድሩ እንደምትሳተፍ ትጠበቅ የነበረችው ጅቡቲ ራሷን አግልላለች። በውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ነገ ወደ ስፍራው የሚያቀና ሲሆን የመጀመሪያ ጨዋታውንም ከነገ በስቲያ ከዩጋንዳ ጋር ያካሂዳል። በሁለት ምድብ ተከፍሎ በሚካሄደው ውድድር አዘጋጇ አገር ኤርትራ፣ ብሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሱዳንና ሶማሊያ በምድብ አንድ፤ ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሩዋንዳ ጋር በምድብ ሁለት ተደልድለዋል። የክፍለ አህጉሩ አገራትን የሚያሳትፈው ይህ ውድድር ከነሐሴ 9 እስከ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በአስመራ ከተማ ይካሄዳል፡፡