በግልገልበለስ ከተማ የመጠጥ ውሃ ችግር የሚፈታ ግንባታ ለመጀመር የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
በግልገልበለስ ከተማ የመጠጥ ውሃ ችግር የሚፈታ ግንባታ ለመጀመር የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

አሶሳ ኢዜአ ነሐሴ 9 / 2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የግልገልበለስ ከተማ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት በ85 ሚሊዮን ብር ለሚካሄድ ግንባታ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡ የክልሉ ውሃ መስኖና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጠይብ መሃመድ አለሚን እንዳሉት ለግንባታው ማስፈጸሚያ ገንዘቡ የተገኘው ከሠላም ሚኒስቴር እና የዘላቂ ልማት ግቦች ፕሮጀክት ነው። በደቂቃ ከ22 ሊትር በላይ ውሃ ማመንጫት የሚያስችል ጥልቅ ጉድጓድ ተቆፍሮ ውሃ መገኘቱን አመልክተዋል፡፡ በሚቀጥው አንድ ዓመት ውስጥ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖች፣ የውሃ መስመር እና ቦኖዎች ግንባታ ተጠናቆ ህብረተሰቡ ውሃ ማግኘት እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡ ግንባታው በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ግልገልበለስ ከተማን እንዲሁም በአቅራቢያው የሚገኙ ገነተማርያም፣ ኤዲዳ እና መንደር ሁለት ቀበሌ የሚገኙ ጨምሮ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። ህብረተሰቡ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ግንባታው በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሚከናወኑ የወሰን ማስከበር ሥራዎችን ያለምንም ወጪ ለመተባር ቃል መግባቱም ተመልክቷል፡፡ የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ተወካይ እና የስራና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አካሻ እስማኤል ግንባታው እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡