ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ለአንድ ጉዞ የሚጠይቀውን ክፍያ 4 ብር አደረገ

ነሐሴ 9/2011 የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫዎች ለሚደረግ አንድ ጉዞ የሚያስከፍለውን ታሪፍ 4 ብር እንዲሆን መወሰኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ። የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ ሥራ የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ለተለያዩ ርቀቶች የተለያየ ታሪፍ ያስከፍላል። ኮርፖሬሽኑ ለአጭር ርቀት 2 ብር፣ ለመካከለኛ ርቀት 4 ብር እንዲሁም ለረጅም ርቀት  6 ብር ታሪፍ የክፍያ ስርዓት ሲጠቀም ነው የቆየው። ሆኖም  ከመጪው ነሐሴ 12 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ በሁሉም ርቀት ለሚደረግ አንድ ጉዞ አራት ብር የትኬት ታሪፍ ብቻ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን ኮርፖሬሽኑ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። የታሪፍ ለውጡ ምቹ የቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት፣ ከትኬት ህትመት ጋር የተያያዙ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ የትኬት ስርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ እንደዚሁም ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም ጠቅሷል። ውሳኔው የተላለፈው ወጥ የሆነ ታሪፍ ስርዓት ለመዘርጋት ይቻል ዘንድ ኮርፖሬሽኑ ያካሄደውን ጥናት መሰረት በማድረግ እንደዚሁም ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር በመምከር መሆኑም በመግለጫው ተመልክቷል። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በየቀኑ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት በሚሰጠው አገልግሎት በየቀኑ እስከ 120 ሺህ መንገደኞችን ያስተናግዳል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ29 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን በማሳፈር ከሶስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱም ተዘግቧል። ከቻይና የገቢና ወጪ ንግድ ባንክ በተገኘ ብድርና በኢትዮጵያ መንግስት በተመደበ 475 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ትራንስፖርት በአፍሪካ በዓይነቱ የመጀመሪያው እንደሆነ ይነገራል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም