ቀጥታ፡

ከመሬት ይዞታ ማስተላለፍ ጋር በተያያዘ የሚወጡ ሕጎች ከሕገ-መንግስቱ ጋር ያለመጣጣም ችግሮች ይገጥማቸዋል

ነሐሴ 9/2011 በክልሎች ከመሬት ይዞታ ማስተላለፍ ጋር በተያያዘ የሚወጡ ሕጎች ከሕገ-መንግስቱ ጋር ያለመጣጣም ችግሮች እንደሚገጥማቸው አንድ ጥናት አመለከተ፡፡ ''የመሬት ይዞታ ስለሚተላለፍበት ሁኔታ ከአገሪቱ ሕገ-መንግስት አንፃር''  በሚል የተዘጋጀ አውደ ጥናት እየተካሔደ ነው። ለሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ በመሬት ይዞታ ምክንያት የሚመጡ ቅሬታዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸውን ጥናቱ በቀረበበት ወቅት ተገልጿል። ባለፉት አራት አመታት ከቀረቡት የሕገ-መንግስት ትርጉም ጥያቄዎች ውስጥ አብዛኞቹ ከመሬት ይዞታዎች ጋር የተያያዙ እንደሆነም ተጠቁሟል። ጥናቱን ያቀረቡት የሕገ-መንግስት አስተምሕሮ ቡድን መሪ አቶ ያደታ ግዛው እንዳሉት፤ በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች ከመሬት ይዞታ ማስተላለፍ ጋር ተያይዞ ባሉ ሕጎች ጥናት ተካሒዷል። በውርስ፣ በኪራይና በስጦታ የሚተላለፉ መሬቶችን አስመልክቶ በፌዴራል ደረጃ ጥቅል ሕግ ያለ ሲሆን ክልሎች እንደ ሁኔታው ከዚህ በመነሳት የሚመሩበትን ሕግ እንደሚያወጡ ሕገ መንግስቱ አንቀጽ 40 ላይ ተቀምጧል። ክልሎች በፌዴራል ደረጃ የወጣውን መሬት የመጠቀም መብት ሲተረጉሙ ዝርዝር ሕግ በግልጽ ለማስቀመጥ ሲያዳግታቸው እንደሚታይ ገልጸዋል። ''የአገሪቱ ሕገመንግስት መሬትን መሸጥ የሚከለክል ቢሆንም ባለይዞታው በውርስና በኪራይ እንዲያስተላልፍ ይፈቅዳል'' ብለዋል። ነገር ግን ክልሎች ያስቀመጡት የውርስና የኪራይ መንገድ መሬትን ለመሸጥ የሚያስችሉ እድሎችን ያመቻቻል ነው የተባለው። የገጠር መሬትን በማከራየት ረገድ ለምን ያሕል ጊዜ መከራየት እንዳለበት ገደብ ማስቀመጥ የሚገባ ቢሆንም ክልሎች ገደቡን ወጥ በሆነ መንገድ ባለማስቀመጣቸው አርሶ አደሩ የመሸጥና የመለወጥ ተግባር ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ መሆኑም ተገልጿል። ከመሬት ማስተላለፍ ጋር ተያይዞ በክልሎች የሚወጡ ዝርዝር ሕጎች ክፍተት እንዳለባቸው የተገለፀ ሲሆን ከሕገ-መንግስቱ አንጻር ሲታይ ልዩነት እንዳለበት ተጠቁሟል። እንደምሳሌ የማውረስ መብት ለቤተሰብ አባል ወይም ከባለይዞታው ጋር ተጠግቶ የሚኖር ሰው መሆን እንዳለበት የሚያስቀምጥ ሲሆን ዝርዝር አካሔዶችን በማስቀመጥ ረገድ ክፍተቶች አሉባቸው ተብሏል። ''የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው” በማለት ህገ-መንግስቱ መደንገጉ ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም