የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በ3ኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ለመካፈል ወደ ኡጋንዳ አቀኑ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በ3ኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ለመካፈል ወደ ኡጋንዳ አቀኑ

ነሐሴ 9/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከነሀሴ 8 እስከ 10 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው በ3ኛው የኢትዮጵያ እና የኡጋንዳ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ለመካፈል ወደ ኡጋንዳ ማቅናታቸው ተገለጸ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ሚኒስትሩ ዛሬ ነሀሴ 09 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ካምፓላ አቅንተዋል፡፡ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ በፖለቲካ፣ በደህንነት፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ማድረጋቸው ይታወቃል። እነዚህን የትብብር ዘርፎች ለመተግበር የሚያስችል የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እ.ኤ.አ. ሐምሌ 22 ቀን 2011 ተፈራርመው ወደ ሥራ መግባታቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ የመጀመሪያው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በኡጋንዳ ካምፓላ፣ ሁለተኛው በአዲስ አበባ መካሄዳቸውን ገልጿል። በሁለቱ አገሮች መሪዎች ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ወደ ኡጋንዳ እንዲሁም ከኡጋንዳ ወደኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ጉብኝቶች የተካሄዱ ሲሆን በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ሚኒስቴሩ አመልክቷል። ሁለቱ አገሮች አባል በሆኑባቸው ዓለም አቀፍና ክልላዊ መድረኮች በመቀራረብና ተመሳሳይ አቋም በማራመድ በመሥራት ላይ እንደሚገኙም ጠቁሟል። በተለየ መልኩ የተመሰረተው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን የትብብር ማዕቀፍ ሁለቱ አገሮች ተቀራርበውና አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለይተው በጋራ እንዲሰሩ አግዟል። በአሁኑ የ3ኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የተለያዩ ስምምነቶች ይፈረማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በኦፊሲላዊ ደረጃ ግንኙነት የጀመሩት በ1956 ዓ.ም ሲሆን ኡጋንዳ በ1962 ዓ.ም ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ከፍታለች። ኢትዮጵያ በ1987 ዓ.ም በቆንስላ ደረጃ በመክፈት በዓመቱ በ1988 ዓ.ም ወደ ኤምባሲ በማሳደግ ግንኙነቱን የማጠናከር ስራ ሰርታለች።